ኢትዮጵያ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እና በኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ እምርታ ላይ ትገኛለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እና በኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ እምርታ ላይ ትገኛለች
አዲስ አበባ፤ ነሃሴ 1/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እና በኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ እምርታ ላይ እንደምትገኝ በብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ስሁል ገለጹ።
ብልፅግና ፓርቲ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በማስመልከት ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ማብራሪያ ሰጥቷል።
የብልፅግና ፓርቲ የህዝብ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፣ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ ያደረጉ አምባሳደሮች እንዲሁም የተለያዩ የዲፕሎማቲክ ማሕበረሰብ አባላት በማብራሪያው ወቅት ተገኝተዋል።
በብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ስሁል በዚሁ ወቅት ባቀረቡት ማብራሪያ፤ የምርጫ ሂደቱ በሦስት ዋና ዋና ደረጃዎች ተከፍሎ የተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫው ከመካሄዱ አንድ ዓመት በፊት ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው የዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን ተናግረዋል።
በዚህም በመገናኛ ብዙኃን፣ በየደረጃው በሚገኙ የፓርቲ አወቃቀሮችና የማህበረሰብ ንቅናቄዎች አማካኝነት ሰፊ የምርጫና የዜግነት ትምህርት ሲሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል።
በምርጫው ዕለት ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ የተመዘገበበትና ሰላማዊ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት መካሄዱን ገልጸዋል።
በበርካታ የምርጫ ጣቢያዎች እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ረጅም ሰልፎች የታዩ መሆኑን አውስተው፤ የምርጫ ተቋማት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ታዛቢዎች እንዲሁም የፀጥታ አካላት በቅንጅት መስራታቸውን ገልጸዋል።
ከምርጫ በኋላ ሕዝቡ የምርጫ ውጤት ማረጋገጫና ይፋ ማድረጊያ የሁለት ሳምንት ጊዜን በትዕግስት መጠባበቁን ጠቁመው፤ ይህም የተቋማትን መገንባትና የህዝቡን ዴሞክራሲ ብስለት ያሳየ ነው ብለዋል።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከ54 ሚሊዮን በላይ መራጮች የተመዘገቡ መሆኑን አስታውሰው፤ በዚህም 94 በመቶ መራጮች ድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ላይ መሣተፋቸውን ተናግረዋል።
በአጠቃላይ 501 የምርጫ ክልሎች እና 52,000 የምርጫ ጣቢያዎች እንደነበሩ አውስተው፤ በምርጫ ዕለት ከ195 ሺህ በላይ የምርጫ አስፈፃሚዎች መሰማራታቸውን ተናግረዋል።
በመራጮች ምዝገባ ወቅት ደግሞ 187 ሺህ ባለሙያዎች ተሳታፊ መሆናቸው የተቋማትን አቅም ያሳያል ብለዋል።
በምርጫው 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች 10 ሺህ 934 ዕጩዎች መወዳደራቸውን ጠቅሰው፤ ከእነዚህም መካከል 2 ሺህ 198 የፌዴራል፣ 8 ሺህ 736 የክልል እና ከተማ አስተዳደር ዕጩዎች እንዲሁም 73 የግል ተወዳዳሪዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በምርጫው ሂደት ከ64 በላይ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የተወጣጡ 1 ሺህ 814 የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፣ 169 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና 55 እውቅና የተሰጣቸው የሀገር ውስጥ ታዛቢ ድርጅቶች መሳተፋቸውን ጠቁመዋል።
ከዓለም አቀፍ ታዛቢዎች አኳያም 73 አባላት ያሉት የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን፣ 26 የኢጋድ አጭር ጊዜ ታዛቢዎች እና በርካታ አዲስ አበባ የሚገኙ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ታዛቢዎች ሂደቱን መታዘባቸውን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እና በኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ እምርታ ላይ ትገኛለች ያሉት የፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ፤ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ማሸነፏን ተናግረዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከ501 ውስጥ 438ቱን መቀመጫዎች ማግኘቱን ጠቅሰው ከክልል ምክር ቤት 2ሺህ 700 መቀመጫዎች ውስጥም 2ሺህ 410 መቀመጫዎች ማግኘቱን ጠቅሰዋል።
በሌላ መልኩም 8 የተፎካካሪ ፓርቲዎች መቀመጫ ማግኘታቸውን ጠቅሰው በዚህም 49 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን እና 246 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎችን ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።