ቀጥታ፡

የቁልፍ መሰረተ ልማቶች የሳይበር ደህንነት አዋጅ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም መከበር ጉልህ ሚና ይኖረዋል

አዲስ አበባ፤ ነሃሴ 1/2018 (ኢዜአ)፦የቁልፍ መሰረተ ልማቶች የሳይበር ደህንነት አዋጅ የሳይበር ደህንነትን በማረጋገጥ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም መከበር ጉልህ ሚና እንደሚኖረው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ ገለጹ።

ዋና ዳይሬክተሯ ትዕግስት ሃሚድ አዋጁን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም፤ አዋጁ  ሰኔ 2 ቀን 2018 ዓ ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁን ጠቅሰዋል።

ቁልፍ መሰረተ ልማቶች ጥበቃ የኢትዮጵያን የዲጂታል ሽግግር ጉዞ በጠንካራ የሳይበር ደህንነት መሰረት ላይ ለመገንባት የሚያስችል መሆኑንም አንስተዋል። 

የዲጂታል መታወቂያ መርሃ ግብር፣ የሞባይል ክፍያና የኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓት እና መሰል ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ መጠን ያለው ዳታ እንደሚያመነጩ አመልክተው፤የእነዚህን መረጃዎች እና ሲስተሞች ደህንነት ማረጋገጥ ወሳኝ ነው ብለዋል።

በመሆኑም የአዋጁ ወደ ስራ መግባት የሳይበር ደህንነትን ማረጋገጥ የዜጎች እና የሀገርን መረጃ ከጥቃት በመጠበቅ የመረጃ ሉዐለዊነትን ለማረጋገጥ ትልቅ እርምጃ መሆኑን አብራርተዋል።

በቁልፍ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚቃጡ ጥቃቶች እየጨመረ መምጣት ለአዋጁ መውጣት ምክንያት መሆኑን ገልጸው፤አዲሱ አዋጅ የሳይበር  ስጋትን መሰረት ያደረገ ቁጥጥር እና የተማከለ  የክስተት ምላሽ  ስርአትን  ለመዘርጋት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በአዋጁ መሰረት አስተዳደሩ ቁልፍ መሰረተ ልማት ተቋማት ማሟላት በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉ ማገዝ ፣ ለቁልፍ መሰረተ ልማቶች ጥበቃ የሚረዱ መመሪያዎችና ስታንዳርዶችን ማዘጋጀት በህግ ማዕቀፉ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል እንደሚገኝበት አክለዋል።

በቁልፍ መሰረተ ልማት ጥበቃ ዙሪያ ብቁ ባለሙያና በስነ ምግባር የታነጸ የሰው  ሃይል  የማደረጀት ስራዎች ይሰራሉም ብለዋል።

በአዋጁ ዙሪያ ለህብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ የማስጨበጥ ተግባራት እንደሚከናወኑም ገልጸዋል።

ቁልፍ  መሰረተ ልማት ባለቤት የሆኑ ተቋማት ደግሞ የሰለጠነ ባለሙያ ማሰማራት፣ማብቃት እና ተገቢውን ደህንነት ማጣሪያ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አዋጁ እንደሚደነግግም ጠቁመዋል።

ከሳይበር ጥቃት ራሳቸውን መጠበቅ የሚችሉበት ቴክኖሎጂዎችን መታጠቅ ከተቋማቱ የሚጠበቅ ሌላው ሃላፊነት መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም