ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት የአፍሪካ ኃያል ሀገር እየሆነች ነው-ታዋቂው የህንድ ሚዲያ ፈርስት ፖስት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት የአፍሪካ ኃያል ሀገር እየሆነች ነው-ታዋቂው የህንድ ሚዲያ ፈርስት ፖስት
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 1/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መሪነት የመጪው ዘመን የአፍሪካ ኃያል ሀገር ወደመሆን እየተሸጋገረች ነው ሲል ታዋቂው የህንድ ሚዲያ ፈርስት ፖስት ዘግቧል።
ፈርስት ፖስት ሚዲያ ኢትዮጵያን በተመለከተ በሠራው ትንታኔው የሰው ዘር መገኛ፣የጥንታዊ መንግስታት ምድር፣የንግድ መስመሮች እና ከፍ ያለ የአፍሪካ ታሪካዊ መሰረት ያላት ሀገር መሆኗን አውስቷል።
ሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ከቀድሞ ገናና ታሪኳ እኩል ታላቅ የሆነ አዲስ ምዕራፍ ለመገንባት በትጋት ላይ መሆኗን አንስቷል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት በቀጣናው እና የአፍሪካ ኃያል ሀገር መሆን የሚያስችላትን እንዲሁም የአህጉሪቱን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚበይንና የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት እየሠራች መሆኗንም እንዲሁ።
ለረጅም ዓመታት ዓለም ኢትዮጵያን የሚያውቃት በጦርነት፣በድርቅ እና በፖለቲካዊ አለመረጋጋት እንደነበር በማስታወስ፥ዛሬ ግን ሀገሪቱ ይህንን የተዛባ ትርክት በኢነርጂ መሠረተ ልማት፣ በአቪየሽን፣ በማዕድን እና በዲጂታል ኢኮኖሚ አስደማሚ ለውጦች ለመቀየር እየሠራች ነው ብሏል።
ኢትዮጵያ ፈተናዎችን ተሻግራ እንዴት በአፍሪካ ፈጣን ዕድገት ካላቸው ኢኮኖሚዎች ቀዳሚዋ ሆና ልትቀጥል ቻለች? የሚለውን ጥያቄ በማንሳትም በዝርዝር መልሶቹን ያብራራል።
የዚህ ዋና ጥያቄ ዝርዝር ምላሽ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት እየተተገበሩ የሚገኙ የኢትዮጵያን የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወስኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ ነው ያለው ሲል አንስቷል።
• የመጀመሪያው የኢነርጂ አብዮት እና ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ነው።
በዚህ የኢትዮጵያ የለውጥ ጉዞ ጎልቶ የሚነሳው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሲሆን፣ ከ5 ሺህ ሜጋዋት በላይ የማመንጨት አቅም ያለው የአፍሪካ ትልቁ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀክት መሆኑን ፈርስት ፖስት በዘገባው ጠቅሷል።
ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ መሻቶች መሰረት፣የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የውጭ ምንዛሬ እና የቀጣናዊ ተጽዕኖ መፍጠሪያ አቅም መሆኑንም አብራርቷል።
የሕዳሴ ግድብ ልዩ የሚያደርገው የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ከዓለም ባንክ ወይም ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አንድ ሳንቲም ሳይበደር በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ደም፣ ላብና ገንዘብ የተገነባ አፍሪካውያን በራሳቸው ህልማቸውን ማሳካት እንደሚችሉ ያሳየነው ብሏል።
ለኢትዮጵያውያን ግድቡ ከኮንክሪት እና ከተርባይን በላይ ትርጉም አለው ያለው ይህ የፈርስት ፖስት ዘገባ፥ እጅግ የላቀ እራስን የመቻል እና የኢኮኖሚ ነፃነት ማሳያ ሐውልት መሆኑንም ተንትኗል።
ኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይልን ለኬንያ፣ ለጂቡቲ እና ለሱዳን በመሸጥ ኤሌክትሪክን ወደ ከፍተኛ ገቢ ማመንጫነት እየቀየረች ከመሆኑም በላይ የመላው ምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ የትስስር ማዕከል ሆናለች ነው ያለው።
• የኢትዮጵያ የዕድገት ምሰሶ አቪዬሽን እና ቀጣናዊ ትስስር
ኢነርጂ ብቻውን ኢኮኖሚያዊ አቅምን አይገነባም፤ ይልቁንም ኢነርጂ ኢንዱስትሪን ያነቃቃል፣ ትስስር ዓለም አቀፍ ንግድን ይመግባል ያለው ፈርስት ፖስት፥የአፍሪካ ግዙፉ አየር መንገድ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን ለላቀ የዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ጉዞ መጀመሩን አንስቷል።
በ12 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ግንባታው እየተፋጠነ የሚገኘው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በየዓመቱ እስከ 110 ሚሊዮን ተጓዦችን እና ወደ 4 ሚሊዮን ቶን የሚጠጋ የዕቃ ጭነት ማስተናገድ አቅም አለው።
ሙሉ በሙሉ ግንባታው ሲጠናቀቅም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከታላላቅ የአቪዬሽን ማዕከላት አንዱ ይሆናል ብሏል።
ይህ ፕሮጀክት የአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የዲፕሎማሲ መናኸሪያ የሆነችውን አዲስ አበባንና አፍሪካን፣ከሌሎች የዓለም ክፍሎች የሚያስተሳስር ዋና የመተላለፊያ ማዕከል እንደሚሆንም ተገልጿል።
ስለዚህ አዲሱ የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ለንግድ፣ ለኢንቨስትመንት እና ለቱሪዝም፣ ለዓለም የዲፕሎሲ ትብብር ጉልህ ሚና እንዲያበረክት ታስቦ እየተገነባ ነው ብሏል።
• የማዕድን ኢንቨስትመንትና በምግብ ራስን መቻል
በሌላ በኩል ከኢትዮጵያ መሬት በታች ላለው የማዕድን ሀብቷ ትኩረት በመስጠት የልማት አብዮት እያካሄደች ስለመሆኑም ተንትኗል።
ሀገሪቱ የወርቅና ሌሎች ማዕድናት ማውጫ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በማስፋፋት አዳዲስ የውጭ ምንዛሬ ምንጮችን እያፈራች የማዕድን ኢንዱስትሪዋን እያሳደገች ነው።
ወርቅ በፍጥነት ከኢትዮጵያ ቀዳሚ የወጪ ንግድ ምርቶች አንዱ በመሆን ለረጅም ጊዜ በግብርና ላይ ብቻ ጥገኛ ሆኖ የቆየውን ኢኮኖሚ ወደ ብዝኃ ዘርፍ እያሸጋገረ ይገኛል።
በሌላ በኩል በምግብ ራስን ከመቻል ውጭ የትኛውም ኢኮኖሚያዊ ለውጥ የተሟላ ሊሆን አይችልም ያለው የፈረስት ፖስት ዘገባ፥ ግብርና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት መሆኑን ጠቅሷል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የሚመራው መንግሥት ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን እንድትችል በጀመረው የለውጥ ጉዞ አስደማሚ ውጤት እያመጣ ነው ብሏል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም ከጉባ ብስራቶች አንዱ የሆነውና በሶማሌ ክልል እየተገነባ የሚገኘው የማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክት በየዓመቱ 3 ሚሊዮን ቶን የሚጠጋ ዩሪያ ማዳበሪያ ማምረት የሚችል ነው።
ይህም ከውጭ የሚገባውን ማዳበሪያ ጥገኝነት በመቀነስ የኢትዮጵያን የግብርና ምርታማነት ለማሳደግ እንደሚያስችል አብራርቷል።
"የምግብ ዋስትና የእኛ ስትራቴጂካዊ ጣልቃ ገብነት ነው።ያንን ግብ እውን ለማድረግ ግብአቶች ላይ መስራት አለብን።በግብአት ላይ መስራት ካልተቻለ የምግብ ዋስትናን እውን ለማድረግ መንገድ የለውም" የሚለውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ በማካተት ዘገባው ሰፊ ሽፋን ሰጥቷል።
ዲጂታላይዜሽን እና የኢንቨትመንትና የገበያ ማሻሻያዎች
በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ለውጥ ወደ ዲጂታልም እየተሸጋገረ ነው።ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እንደተናገሩት የ5 ሚሊዮን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ስልጠና ከዕቅዱ ቀድም ከመሳካቱም በላይ በርካታ ወጣቶች የዲጂታል እውቀት ባለቤት አድርጓል።
በተመሳሳይ የዲጂታል ትስስር እየሰፋ ሲሆን የ4ጂ እና 5ጂ አገልግሎቶች በበርካታ ከተሞች ተደራሽ ሆኗል።
ኢትዮጵያ ለበርካታ አስርት ዓመታት ተዘግተው የቆዩ እንደ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ ባንክ እና የካፒታል ገበያዎች ያሉ ዘርፎችን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ማድረጓንም አድንቋል።
የካፒታል ገበያን መጀመሯም የግል ካፒታል ልውውጥን በማጎልበት ለኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ተንትኗል።
እነዚህ ማሻሻያዎች በአጠቃላይ በመንግስት ቁጥጥር ስር ከነበረው የኢኮኖሚ ወደ ግል ዘርፍ ኢንቨስትመንት እያደገ የሚሄድ ኢኮኖሚ መሰረታዊ ለውጥን እየተገነባ መሆኑን ያሳያሉ ነው ያለው።
ኢትዮጵያ ካላት የጂኦ ፖለቲካ ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ አኳያ እድልና ፈተናዎች ከፊቷ መሆናቸውን በማንሳት፥ አዲሱን የዓለም አቀፍ የትብብር ጥምረት ብሪክስ አባል መሆኗን አውስቷል።
ከቻይና፣ ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት፣ ከምዕራባውያን አጋሮችና ከአፍሪካ ኢንቨስተሮች ኢንቨስትመንትን እየሳበች እንደምትገኝም እንዲሁ።
ኢትዮጵያ ጎራ ሳትለይ ከሁሉም የዓለም ሀገራት ጋር ትብብሯን እያጠናከረች ነው ብሏል።
ዓለም ኢትዮጵያን የምታስታውሰው በጦርነት ቢሆንም፥ኢትዮጵያ ዓለም በአዲሱ የለውጥና የስኬት ጉዞዋ እንዲያስታውሳት እየሠራች ነው።
ለዚህም በመላው ሀገሪቱ በሁሉም ዘርፍ ግዙፍ የኢኮኖሚ ሽግግር እየተካሄደ ሲሆን፥ ይህ የኢትዮጵያ ጉዞ ለቀጣዮቹ ዓመታት የቀጣናውንና የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊና አጠቃላይ ገጽታ በአዲስ መልኩ የሚቀርጽ ነው ሲል ፈርስት ፖስት ዘገባውን አብራርቷል።