የምክክር ጉባኤው አለመግባባቶችን በመፍታት ዘላቂ ሰላምና ልማትን ያመጣል - ኢዜአ አማርኛ
የምክክር ጉባኤው አለመግባባቶችን በመፍታት ዘላቂ ሰላምና ልማትን ያመጣል
አሶሳ፤ ነሃሴ 1/2018 (ኢዜአ)፦የምክክር ጉባኤው ይስተዋሉ የነበሩ አለመግባባቶችን በመፍታት ዘላቂ ሰላምና ልማትን እንደሚያመጣ ተስፋ ማድረጋቸውን የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለምክክር በተለዩ አጀንዳዎች ላይ በምክክር ጉባዔው የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍል ተወካዮችን እያወያየ ይገኛል።
ነዋሪዎቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ ተወያዮች በምክክር ጉባኤው በጥልቀት በመወያየት የኢትዮጵያን አሸናፊነት የሚያበስር ሐሳብ ይዘው እንደሚወጡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የምክክር ጉባኤው ይስተዋሉ የነበሩ አለመግባባቶችን በመፍታት ዘላቂ ሰላምና ልማትን እንደሚያመጣ ተስፋ ማድረጋቸውንም ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ወሊድ አንዋር እንደገለጹት፤ የምክክር ጉባኤው በሀገሪቱ ሲስተዋሉ የነበሩ አለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላምና ልማትን ያመጣል ብለዋል።
ወይዘሮ መብራቴ ገረመው በበኩላቸው፤ ምክክሩ ኢትዮጵያውያን የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለማጎልበትና በውይይት ችግሮች የሚፈቱበትን አዲስ የፖለቲካና ማኅበራዊ ሥሪት ለመገንባት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሁሉንም በአንድ መድረክ ያሰባሰበ መሆኑ ሀገራዊ መግባባትን ለማሳካት የራሱ ድርሻ አለው ያሉት ደግሞ አቶ ሐመደነላህ አብደላህ ናቸው።
ምክክሩ ቀጣይነት ላለው ዕድገትና ብልፅግና ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም ገልጸዋል።