የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት 67 ቢሊዮን ብር በጀት አፀደቀ - ኢዜአ አማርኛ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት 67 ቢሊዮን ብር በጀት አፀደቀ
ወልቂጤ፤ ነሃሴ 1/2018 (ኢዜአ)፦የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ለ2019 በጀት ዓመት 67 ቢሊዮን ብር በጀት አፀደቀ።
ምክር ቤቱ በጀቱን ዛሬ ያጸደቀው በወልቂጤ ከተማ እያካሄደ ባለው 6ኛ ዙር፣ 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ስድስተኛ መደበኛ ጉባኤው ነው፡፡
በምክር ቤቱ የፕላን፣ መሰረተ ልማትና የመንግስት ሃብት ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ታመነ ገብሬ የክልሉ መንግስት የ2019 ረቂቅ በጀት 67 ቢሊዮን ብር መሆኑን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
በጀቱ በክልሉ ከውስጥ ገቢ በሚሰበሰብ እና ከፌደራል መንግስት በሚመደብ በጀት የሚሸፈን መሆኑንም ገልጸዋል።
የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ ዘይቱና ኢብራሒም በበኩላቸው በጀቱ የክልሉን የልማት ፍላጎት ለማሳደግ ታሳቢ ተደርጎ የተመደበ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በተለይ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እንዲሁም የሕዝብን የመሰረተ ልማት ጥያቄ መመለስ ለሚችሉ የልማት ሥራዎች ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በጀቱ በገጠር እና በከተማ ለአዳዲስ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለመስኖ ልማት እንዲሁም የተጀመሩ እና ቀጣይ በአዲስ ለሚሰሩ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ እንደሚውል አመልክተዋል።
ምክር ቤቱ በቀረበው የክልሉ የ2019 ረቂቅ በጀት ላይ ከተወያየ በኋላ አጽድቋል።