የአንድ ጀምበር አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የህዝብን አቅም በማስተባበር የተከናወነ ታሪካዊ ስኬት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአንድ ጀምበር አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የህዝብን አቅም በማስተባበር የተከናወነ ታሪካዊ ስኬት ነው
ጅማ ፤ ነሃሴ 1/2018 (ኢዜአ)፦ የአንድ ጀምበር አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በመደመር መንግስት እሳቤ የህዝብ አቅምን በማስተባበር የተከናወነ ታሪካዊ ስኬት መሆኑን የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
የመደመር መንግሥት የተበታተነን አቅም በማቀናጀትና የዜጎችን ንቁ ተሳትፎ በማጎልበት፣ በአንድ ቀን ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን መትከልን የመሰሉ በተግባር የተገለፁና የሚገለፁ እውነታዎችን የያዘ እሳቤ ነው።
ይህም የኢትዮጵያውያን በጋራ መቆም፣ የውስጥ አቅምን አሟጦ መጠቀም እና የትብብር ባህልን ማሳደግ አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣት እንደሚያስችል በተግባር ያረጋገጠና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጉዞ የሚያፋጥን ነው።
ምሁራኑ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት እንደገለፁት፤ የአንድ ጀምበር አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በመደመር መንግሥት እሳቤ የሕዝብ አቅምን በማስተባበር የተከናወነ ታሪካዊ ስኬት ነው።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር ጌታቸው ጥላሁን (ዶ/ር) ፤ የአንድ ጀምበር አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በመደመር መንግሥት እሳቤ የሕዝብ አቅምን በማስተባበር የተከናወነ ታሪካዊ ስኬት ነው ብለዋል።
ይህንንም ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ለሀገራዊ ጥሪው ስኬት የድርሻውን በመወጣት ማሳየቱን ተናግረው ከመንግሥት ጎን በመቆምም ለኢኮኖሚው ዕድገት ያለውን ቁርጠኝነት መግለፁን ጠቁመዋል።
ሕዝቡ በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ ያሳየውን የተቀናጀ መረዳዳትና ከፍተኛ ተሳትፎ፣ በሀገር ግንባታ፣ በኢኮኖሚ ዕድገት እንዲሁም በሕብረተሰብ አቀፍ በጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ ማስቀጠል የሚገባው መሆኑን አስረድተዋል።
ባለፉት ዓመታት እየጎለበቱ የመጡትን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እና የማዕድ የማጋራት እንቅስቃሴዎችን በምሳሌነት የጠቀሱት ምሁሩ፤ በጥቂቱ ታስቦ የተጀመረው ሥራ ትልቅ ደረጃ መድረስ እንደሚችል ማሳያ ነው ብለዋል።
በተለይም በሁሉም ዘርፎች የተጀመሩ ዘላቂ የልማት ስራዎችን ከዳር ለማድረስ የዜጎች ሕብረትና አንድነት ወሳኝ መሆኑን የጠቆሙት ምሁሩ፤ ይህ የሕዝቡ ቀናነትና ለልማት የመቆም ባህል በሁሉም መስክ ሊስፋፋ እንደሚገባም አመልክተዋል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ሥነ-ምግብ መምህርና ተመራማሪ ዋሲሁን ሀሰን (ዶ/ር)፤ የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ትልቅ ሀገራዊ ድል በመሆኑ፣ ኢትዮጵያውያን በጋራ በመቆም የተቀዳጁትን የዓድዋን ድል የሚያስታውስ ነው ብለዋል።
ሕዝባዊ ትብብርና መግባባት በሚገባ ከተፈጠረ በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ገልፀው ይህንንም ለሀገር ዕድገትና ብልፅግና ማዋል እንደሚገባ ጠቁመዋል።