ሀገራዊ ምክክሩ ሥር የሰደዱ ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ ሥር የሰደዱ ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ያስችላል
ቦንጋ፤ ነሃሴ 1/2018 (ኢዜአ)፦ሀገራዊ ምክክሩ ሥር የሰደዱ ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ሰላሟ የጸና ጠንካራ ሀገር መገንባት እንደሚያስችል የካፋ ዞን የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።
በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ ባለው የምክክር ጉባኤ የህብረተሰብ ተወካዮች በስምንት የምክክር አጀንዳዎች ላይ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እየመከሩ ይገኛሉ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የካፋ ዞን የሀገር ሽማግሌዎች ምክክሩ የቆዩና ሥር የሰደዱ ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት ሰላሟ የጸና ጠንካራ ሀገር ለመገንባት መሰረት ይጥላል ብለዋል።
በዞኑ የቦንጋ ከተማ የሀገር ሽማግሌ ወርቁ ወልደማርያም፤ ሀገራዊ ምክክሩ ከዚህ ቀደም የነበሩና አሁንም ድረስ ሳይፈቱ የቆዩ አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ መክሮ ለመፍታትና ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል።
ምክክሩ ትውልዱ አብሮነቱን የሚያጠናክርበትና በሀገሩ ጉዳይ እኩል የሚወስንበትን ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ተናግረዋል።
እንደ ሀገር ሽማግሌው ገለጻ፣ ሁሉንም አሳታፊና አካታች በሆነ መልኩ እየተካሄደ ያለው ምክክር የቆዩ ሀገራዊ ችግሮችን በውይይት በመፍታት ጠንካራ ሀገር ለትውልድ ለመገንባት ወርቃማ ዕድል ነው።
በካፋ ዞን የጊምቦ ወረዳ ኡፋ ከተማ ሀገር ሽማግሌ ጊምቤራሻ መለሰ መሸሻ በበኩላቸው፣ ሀገራዊ ምክክሩ በህዝቦች መካከል አንድነትን የሚያጠናክር ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ የሚመክሩበትና ሀሳብ የሚለዋወጡበት ምቹ ምህዳር ባለመፈጠሩ አለመግባባቶችን በሀይል ለመፍታት መሞከር ባህል ሆኖ ቆይቷል ያሉት የሀገር ሽማግሌው፣ ምክክሩ ይህን ታሪክ ይቀይራል ብለዋል።
ለዘመናት የቆዩ ችግሮችን ለመፍታት ኢትዮጵያውያን በጋራ ቁጭ ብለው መምከራቸው ታሪካዊ ዕድል መሆኑን ጠቅሰው፣ በኮሚሽኑ የተለዩ የውይይት አጀንዳዎች በየደረጃው በህዝብ የተነሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በምክክሩ የመጨረሻ ምዕራፍ ጉባኤ ላይ የተለያየ አመለካከት፣ ፍላጎት፣ እምነትና ባህል ያላቸው ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ጉዳይ በጋራ ሲመክሩ መመልከት መታደል መሆኑንም ገልፀዋል።