ቀጥታ፡

በምዕራብ ሸዋ ዞን ከ184 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በኩታ-ገጠም አሰራር በበቆሎ ሰብል እየለማ ነው

አምቦ ፤ ነሃሴ 1/2018 (ኢዜአ)፦ በምዕራብ ሸዋ ዞን በዘንድሮው የመኸር ወቅት ከ184 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በኩታ-ገጠም አሰራር በበቆሎ ሰብል እየለማ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ።

በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ሸዋ ዞን፣ ለእርሻ ስራ ተስማሚ በሆነው አየር ንብረቱ እና ለም አፈር ምክንያት ከሀገሪቱ ዋነኛ የሰብል አምራች አካባቢዎች አንዱ ነው። 

በዞኑ ከሚመረቱት ዋና ዋና ሰብሎች መካከል በቆሎ የመጀመሪያውን ደረጃ የሚይዝ ሲሆን፣ ለአካባቢው አባወራዎች የምግብ ዋስትና እና ገቢ ማግኛ ዋነኛ መሰረት ነው።

በክልሉ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተዘረጋው የኩታ-ገጠም የእርሻ አሰራር አነስተኛ አራሾች መሬታቸውን አስተባብረው በጋራ እንዲያርሱ የሚያስችል ስልት ነው። 


 

ይህ አሰራርም የቴክኖሎጂ እና ግብአት አጠቃቀምን ለማሳደግ፣ ምርታማነትን ለመጨመርና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ጉልህ ድርሻ አለው።

የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፍ አቶ ተረፈ አራርሳ ለኢዜአ እንዳስታወቁት፤ በ2108/19 የመኸር ወቅት 219 ሺህ 767 ሄክታር መሬት በበቆሎ ሰብል ለመሸፈን ታቅዶ  ከእቅድ በላይ  226 ሺህ 788 ሄክታር ማልማት ተችሏል።


 

ከዚህ ውስጥ ከ184 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው በኩታ-ገጠም(ክላስተር ) እየለማ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በተለይም እንደ ሀገር ድህነትን ለማስወገድና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተነደፉ አቅጣጫዎችን በመከተል፣ በክልሉም በአዳዲስ እሳቤዎች ላይ የተመሰረቱ ሀሳቦችን ወደ ተግባር ለመለወጥ የተቀናጀ የህዝብና የአመራር ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

በዚህ ረገድ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ በማስተዋወቅና በማላመድ፣ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር ለገበያና ለኢንዱስትሪ የሚሆኑ ግብዓቶችን ለማቅረብ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን አውስተዋል።

በምርት ዘመኑ በዞኑ በበቆሎ ሰብል ከተሸፈነው አጠቃላይ መሬት 13 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስረድተዋል።

በዞኑ የኖኖ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወንዳፍራሽ ሉሌሳ እንደገለጹት፤ በዘንድሮው የምርት ዘመን በወረዳው 54 ሺህ 433 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኗል።


 

ከዚህ ውስጥ 26 ሺህ ሄክታር የሚሆነው በበቆሎ ሰብል እየለማ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የወረዳው አርሶ አደሮች በበኩላቸው እንደተናገሩት፣ ከዚህ ቀደም ከአንድ ሄክታር መሬት የሚያገኙት ምርት ከ12 ኩንታል የሚበልጥ አልነበረም።

ዘንድሮ ግን በኩታ-ገጠም (ክላስተር) ካለሙት የበቆሎ ሰብል በሄክታር ከእጥፍ በላይ ምርት ለማግኘት አቅደው አስፈላጊውን እንክብካቤ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከአርሶ አደሮቹ መካከል አቶ ሸለማ ወርቁ  በኩታ-ገጠም አሰራር ዘር መዝራታቸውን ጠቅሰው፣ ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀማቸው የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።


 

ሌላኛው የወረዳው አርሶ አደር ገረሙ ኢዶሳ በበኩላቸው፣ በየዓመቱ በባለሙያ ምክር በመታገዝ በቆሎ በስፋት እንደሚያመርቱና ዘንድሮም የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም