ቀጥታ፡

በዞኑ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ዝግጁ ተደርገዋል

ደብረ ብርሃን ፤ ነሃሴ 1/2018 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ዝግጁ የማድረግ ስራ መከናወኑን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ፀጋዬ እንግዳወርቅ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በአዲሱ የትምህርት ዘመን በቅድመ መደበኛ ትምህርት ላይ በማተኮር የትምህርት ጥራትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ይገኛል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ 93 አዲስ የቅድመ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ዝግጁ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።


 

የተገነቡት ትምህርት ቤቶችም በትምህርት ዘመኑ በቅድመ አንደኛ ደረጃ 97 ሺህ ህፃናትን ተቀብሎ ለማስተማር የተያዘውን ግብ ለማሳካት የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የቡልጋ ከተማ አስተዳደር አንድ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገንብቶ ለመማር ማስተማር ስራው ዝግጁ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።


 

ከዚሁ ጋር በተያያዘም 724 የመማሪያ ክፍሎችን እንዲሁም ወንበርና ጠረጴዛዎችን በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመጠገን ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ከ129 ሺህ በላይ ደብተር፣ ከ962 ፓኮ እስክሪብቶና እርሳስ ለማስባሰብ መቻሉን አስገንዝበዋል።


 

በተጨማሪም የመማሪያ ቁሳቁሶችን በማሟላት እና የትምህርት ቤቶችን ግቢ ሳቢና ማራኪ በማድረግ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

መምህር መኳንንት ታደሰ እንደገለጹት፤ ባለው በጀት ዓመት የተገነባው የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ህጻናትን ከታችኛው የክፍል ደረጃ ጀምሮ አንጾ ለማስተማር ሰፊ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

መምህርት ትግስት ከበደ በበኩላቸው ፤ በክረምቱ የመማሪያ ክፍሎችን፣ ወንበሮችና ጠረጴዛዎችን በመጠገን ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።


 

ለተማሪዎች የመማሪያ ደብተር፣ እስክሪብቶና ሌሎች የትምህርት ቁሳቁሶችን የማሰባሰብ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

በዞኑ ከቅድመ መደበኛ እስከ 2ኛ ደረጃ ባለው የትምህርት እርከን ከ616 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም