ቀጥታ፡

የሕገ -ወጡ ሕወሃትን የጦርነት ቅስቀሳና አፈና ልንታገለው ይገባል - የትግራይ ወጣቶች

አዲስ አበባ፤ ነሃሴ 1/2018 (ኢዜአ)፦የታሪካዊ ጠላቶች ተላላኪ የሆነውን ሕገ-ወጡን የሕወሃት ቡድን የጦርነት ቅስቀሳና አፈና የትግራይ ህዝብና ወጣቶች አጥብቀው ሊቃወሙትና ሊታገሉት እንደሚገባ ከቡድኑ ግፍና አፈና ሸሽተው የመጡ የትግራይ ተወላጅ ወጣቶች ገለጹ።

ሕገ -ወጡ የሕወሃት ቡድን በአሁኑ ወቅት  ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመቀናጀት የትግራይ ወጣቶችን ለጦርነት በግዳጅ እያፈሰና ወደ ሱዳን በመሸጥ አስከፊ ግፍ እየፈጸመ ይገኛል።

በርካታ ወጣቶችም ይህን ግፍ  በመስጋት አካባቢያቸውን ጥለው እየሸሹ  ይገኛሉ።

ወጣት ገብረኪሮስ ሕሉፍ ፤ ሕገ-ወጡ ቡድን እያፈጸመ ያለው የጦርነት ጉሰማና ግፍ በፈጸመው ወንጀል ላለመጠየቅ የሚያደርገው ጥረት መሆኑን ለኢዜአ ተናግሯል።

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የትግራይ ሕዝብን ፍላጎት ለመመለስ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን  አስታውሶ፤  የፌደራል መንግሥትም በስምምነቱ የተቀመጡ ጉዳዮችን ሲፈጽም መቆየቱን ተናግሯል።

በተቃራኒው ሕገ-ወጡ የሕወሃት ቡድን ግን ስምምንቱን በመጣስ  ለትግራይ ህዝብ ጥቅም  ምንም ዓይነት ደንታ እንደሌለው  በተግባር አሳይቷል ነው ያለው።

የትግራይ ሕዝብ የሚሻው ሰላም ቢሆንም፣ ቡድኑ ከሕዝቡ ፍላጎት ውጭ ወጣቶችን በግዳጅ እያፈሰና ጦርነት እየቀሰቀሰ መሆኑንም ነው የተናገረው።
ይህም የቡድኑን ውድቀትና በሕዝቡ ዘንድ ቅቡልነት ማጣቱን ያመላክታል ብሏል።

ሕገ-ወጥ ቡድኑ ከሻዕቢያና ከሌሎች ተላላኪ ሃይሎች ጋር በመሆን ጦርነት በመቀስቀስ የትግራይ ህዝብን ለከፋ ችግር ለመዳረግ እየተንቀሳቀስ መሆኑን የሚናገረው ወጣት ኪሮስ፤ በመሆኑም ይህን ሕገ-ወጥ ቡድን አምርረን ልንታገለው ይገባል ነው ያለው።

ወጣት ፀጋልዑል በርሄ በበኩሉ፤ የትግራይ ህዝብ ሕገ-ወጡ ቡድንን ጦርነትና ውጊያ ይበቃናል በሚል አጥብቆ እየተቃወመው እንደሚገኝ ተናግሯል።

ሕገ-ወጥ ቡድኑ የሚቃወሙትን ወጣቶች ብቻ ሳይሆን ልጆቻችንን ለምንድን ነው የምትወስዱት ብለው ጥያቄ እያነሱ ያሉ እናቶች ላይ ሳይቀር ግፍ እየፈጸመ ይገኛል ብሏል።

የሕገ-ወጡ ቡድን አመራሮች እኛ ካልገዛንና ካልዘረፍን ወጣቱና ሕዝቡ አይኖርም በሚል በተለመደው እኩይ ተግባራቸው መቀጠላቸው የመጨረሻ ውድቀታቸውን የሚያሳይ መሆኑን በማንሳት፤ እኛ ወጣቶች በሕገ ወጥ ቡድኑ ላይ የጀመርነውን ተቃውሞና ትግል አጠናክረን መቀጠል አለብን በማለትም ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም