ቀጥታ፡

የምክክር ጉባዔው ሀገር የምትፀናው በምክክር እንደሆነ ለትውልዱ ለማስረጽ ምቹ ምህዳር የፈጠረ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሃሴ 1/2018 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ እየተካሄደ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ሀገር የምትፀናው በምክክር እና በሃሳብ የበላይነት እንደሆነ ለትውልዱ ለማስረጽ ምቹ ምህዳርን የፈጠረ ነው ሲሉ ተመካካሪዎች ገለፁ።

የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱን ቀጥሏል።

በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ አራት ሺህ የሕዝብ ወኪሎች በስምንት ዐበይት ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ጥልቅና አሳታፊ ምክክር እያካሄዱ ይገኛሉ።

በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው እየተሳተፉ የሚገኙት ተመካካሪዎች ምክክሩ ኢትዮጵያውያን ትውውቃችንን የበለጠ እንድናጠናክር ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል ብለዋል።

ጉባኤው በቡድን በቡድን በመሆን በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ሀሳባቸውን እንዲያካፍሉ፣ ለሀገር ሰላምና ልማት በሚበጁ ጉዳዮች ላይ እንዲያሰላስሉ እንዳስቻላቸውም ገልጸዋል።

አስተያተያየታቸው ከሰጡ ተመካካሪዎች መካከል አቶ ድሪባ ተሾመ ሀገራዊ ምክክሩ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን አካታችነት ያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል።

እኔም እንደ አንድ ዜጋ በምክክሩ በንቃት በመሳተፍ ተወያዮች የሚያነሷቸውን ሀሳቦች በማዳመጥ እኔም ሀሳቤን በነፃነት እየገለፅኩ እገኛለሁ ብለዋል።

ጉባኤው የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በሰከነ መንገድ መመካከር ወሳኝ መሆኑን የተማርንበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በመደማመጥ መመካከር ዘመናዊነት መሆኑንም ነው ተመካካሪ ድሪባ ተሾመ የተናገሩት።

ሌላኛው ተመካካሪ አሸናፊ ድባቤ በበኩላቸው፤ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የመመካከር ልማድ የሌለን በመሆኑ ኢትዮጵያ ለልዩ ልዩ ችግሮች ተጋልጣ ቆይታለች ሲሉ አንስተዋል።

ለቀጣዩ ትውልድ ምቹና የተሻለች ሀገር ለመገንባት እንዲሁም የመመካከርን ባህል ለማዳበር፣ አሁን ላይ እየተመካከርን እንገኛለን ብለዋል።

የምክክር ጉባኤው አካታች በመሆኑ ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የተሻለ አተያይ እንዲኖር እያስቻለ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው ተመካካሪ ጅቢን አህመድ ናቸው።

በምክክሩ ሂደትም ሀሳባቸውን በነፃነት እያንሸራሸሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በቀጣይ በምክክር ሂደቱ ሰላሟና ልማቷ የተረጋገጠባት ኢትዮጵያን ለትውልዱ ለማስተላለፍ ሀገራዊ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

ሌላኛው ተመካካሪ ከሊፋ ሱሌማን በበኩላቸው፤ ምክክሩ ኢትዮጵያ ችግሮቿን በሀይል ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ የምትፈታበትን ምህዳር መፍጠሯን የምናሳይበት ነው ብለዋል።

ሀገርን ማፅናት የሚቻለው በምክክር መሆኑን ለትውልዱ ለማስገንዘብ ምክክሩ እንደሚረዳም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም