ቀጥታ፡

ምክክሩ የእኛ ትውልድ ያጣውን እድል የመለሰ ነው - አምባሳደር ታደለች ኃይለሚካኤል

አዲስ አበባ፤ ነሃሴ 1/2018 (ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ የእኛ ትውልድ ያጣውን እድል የመለሰ ትልቅ አጋጣሚ ነው ሲሉ የቀድሞው የኢሕአፓ ታጋይ እና 'ዳኛው ማነው?' የተሰኘ መፅሐፍ ደራሲ አምባሳደር ታደለች ኃይለሚካኤል ገለጹ።

አምባሳደር ታደለች ኃይለሚካኤል የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አማካሪ ካውንስል አባልም ናቸው።

አምባሳደሯ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የዛ ዘመን ትውልድ ማህበራዊ ፍትህን፣ ኢኮኖሚያዊ እድገት እና በአጠቃላይ ብዙ ነገር ሲጠይቅ እንደነበር አውስተዋል።

ከነበረው ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ሀገርን መውደድ ብቻውን የትም እንደማያደርስ የነበረው የትግል ሂደት ማሳየቱን ጠቅሰው ወደ ፍትህ ሊወሰድ የሚችለው እሳቤ እንዳልነበረ አመልክተዋል።

እኔ ያልኩት ትክክል ነው፣ እኔ ካልኩት ውጭ ያለው ትክክል አይደለም እያለ የሚሄድ አካሄድ መጨረሻ ላይ ራሱን የሚበላ ጉዳይ ሆኖ መገኘቱን አንስተዋል።

ምክክርን አለማሰብ፤ የቡድን እንኳን ምክክር እንኳን ሊደረግ አለመቻሉ ትልቅ ችግር እና ጠባሳን ትቶ ማለፉን ገልጸዋል።

በመሆኑም አሁን የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር በወቅቱ የነበረው ትውልድ የቆጨውን ነገር የሚካስበትና ሀገራዊ ችግሮችን የሚቀርፍበት ትልቅ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግስት እንዲህ አይነቱን ትልቅ መድረክ ለማመቻቸት ያሳየው ፈቃደኝነትና ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን ነው ያነሱት።

ሹንቁሮችንና ቋጠሮዎችን ለማየት ሀገራዊ ምክክር ማድረግ ትልቅ ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ ነገር ነው ብለዋል።

ሰዎች ሃሳባቸውን አንስተው በመወያየት ወደ አንድ የጋራ ስምምነት ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት ትልቅ ታሪካዊ ሂደት እንደሆነ አብራርተዋል።

ኮሚሽኑ ባለፉት አራት ዓመታት አጀንዳዎችን እስከ ታች ወርዶ በመሰብሰብ ያከናወነው ተግባር ስኬታማ መሆኑን በአዲስ አበባ እና በአማራ ክልል በታዘቡት መድረክ ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።

የውይይት ሂደቱና የተዘጋጀበት መንገድ እያንዳንዱ የማህበረሰብ ክፍል እንዲሳተፍ በጥራት የተሰራ መሆኑንና ዝም ብሎ የተከናወነ ሳይሆን ከፍተኛ ጥረት የተደረገበት መሆኑን መስክረዋል።

የምክክር ኮሚሽኑ አባላት፣ የአማካሪ ካውንስል አባላትና ተሳታፊዎች የራሳቸው ጠንካራ ስብዕና፣ እውቀትና ልምድ ያላቸው እንጂ ማንም በፈለገው መንገድ የሚያዟቸው አለመሆናቸውንም ነው ያስገነዘቡት።

በተጨማሪም ወጣቶችን፣ ሴቶችንና አካል ጉዳተኞችን ያካተተ አደረጃጀት በመሆኑ ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር በትጋት የሚሰራና የሁሉንም ድምፅ ያካተተ መሆኑን ነው ያስረዱት።

ይህ የምክክር ሂደት ወደፊት ለሀገሪቱ ትልቅ የመደማመጥና የመነጋገር ባህል እንደሚፈጥር አምባሳደር ታደለች ገልጸዋል።

በጽንፍ ላይ የነበሩ አቋሞች በመደማመጥና በመተጋገዝ ወደ ማዕከል ሲመጡ ማየት መቻሉን አብራርተው፣ መደማመጥንና ልዩነትን ማስተናገድን መለማመዳችን የዲሞክራሲ ስርዓት እድገት ማሳያ ነው ሲሉ ጠቁመዋል።

በውይይቶቹ ላይ የመንግስት መዋቅር፣ የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግሮችን ጨምሮ በርካታ መሰረታዊ ጉዳዮች እየተነሱ በመሆናቸው፤ ዜጎች ሃሳባቸውን በነፃነት የሚገልጹበት ይህ ሂደት ለሀገሪቱ ብሩህ ተስፋን እንደሚያመጣና ለችግሮቿም መፍትሔ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም