ሕዝበ ክርስቲያኑ የፍልሰታን ጾም የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍና ለሰላም በመጸለይ ሊያሳልፍ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ሕዝበ ክርስቲያኑ የፍልሰታን ጾም የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍና ለሰላም በመጸለይ ሊያሳልፍ ይገባል
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 30/2018 (ኢዜአ) ፦ሕዝበ ክርስቲያኑ የፍልሰታን ጾም የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍና ለሰላም በመጸለይ ሊያሳልፍ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አሳሰበች።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ነገ የሚጀመረውን የ2018 ዓ.ም የጾመ ፍልሰታ ሱባኤ በማስመልከት መልእክት አስተላልፈዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በመልዕክታቸው፣ ምዕመናን ከነሐሴ 1 ጀምሮ ለ15 ቀናት የሚጾሙት የፍልሰታ ጾም የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ በመጠበቅና ለእርሱ ያላቸውን ፍቅር በተግባር ለመግለጽ እንደሆነ ገልጸዋል።
ብፁዕነታቸው ምእመናን የጾመ ፍልሰታ ሱባኤን በጸሎትና በንሥሐ ብቻ ሳይሆን፣ የተራቡትን በመመገብ፣ የተቸገሩትን በመርዳት፣ የታረዙትን በማልበስና የተጣሉትን በማስታረቅ በፍቅርና በምሕረት ሊያሳልፉት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተጨማሪም የታመሙትንና የታሰሩትን በመጠየቅ ሱባኤውን በመንፈሳዊ ትሩፋት እንዲያሳልፉ አሳስበዋል።
ምዕመናን በዓለም ላይ የሚስተዋለውን ስጋት እንዲወገድና ሰላም እንዲሰፍን እንዲጸልዩም ጠይቀዋል።