ሻዕቢያ በቀይባህር አፋሮች ላይ ከሚፈፅመው ግፍ ባለፈ ቀጣናውን ለማተራመስ እየሠራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሻዕቢያ በቀይባህር አፋሮች ላይ ከሚፈፅመው ግፍ ባለፈ ቀጣናውን ለማተራመስ እየሠራ ነው
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 30/2018 (ኢዜአ)፦የቀይ ባህር የአፋር ሕዝብ በሻዕቢያ ከፍተኛ ግፍ እየተፈጸመበት መሆኑን የቀይ ባህር አፋር ዲሞክራሲ ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ያሲን መሀመድ ገለፁ።
የፓርቲው የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ያሲን መሀመድ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የቀይባህር የአፋር ሕዝብ ኑሮው የተመሰረተው ከቀይባህር ከሚገኘው ጥቅም ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።
ነገር ግን ባለፉት አስርት ዓመታት በኤርትራ የሚኖረው የቀይ ባህር አፋር ሕዝብ ከቀዬው በግፍ እንዲፈናቀል ሻዕቢያ ከፍተኛ ሴራ በመሸረብ ጭፍጨፋ እየፈጸመ መሆኑንም ገልጸዋል።
የቀይ ባህር አፋር ሕዝብ ከእህትና ወንድም ሕዝቦች ጋር እንዳይገናኝ ከፖለቲካ፣ከኢኮኖሚ፣ ከማህበራዊ ኑሮ እንዲገለል እንዲሁም በትምህርት ወደኋላ እንዲቀር ከፍተኛ ጭቆና እየፈጸመ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የሻዕቢያ ሥርዓት የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመ ነው ያሉት አቶ ያሱን፥ አገዛዙ እያራመደ ያለው ስሁት አካሄድ ለአካባቢው ዘላቂ የሰላም ጠንቅነት ማረጋገጫ መሆኑን አንስተዋል።
የሻዕቢያ አገዛዝ ከጥቂት ፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር ፅምዶ የሚል እኩይ ጥምረት በመፍጠር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የተናገሩት ያሲን መሀመድ በዚህም ቀጣናውን ለማተራመስ እየሠራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ዛሬ ላይ የተለያዩ ፀረ ሰላም ኃይሎችን በመያዝ ለጥፋት በአስመራ እየተሰባሰበ እንደሚገኝና በዚህም በቀጠናው ዘላቂ ሰላም እንዳይኖር ከፍተኛ ስራ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የቀይ ባሕር አፋር ዴሞክራሲ ፓርቲ ይህ ፀረ ለውጥና ፀረ ልማት የሆነ አምባገነን አገዛዝ መወገድ አለበት በሚል የፀና አቋም እየታገለ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ሥርዓት እስካልተወገደ ድረስ በኤርትራም ሆነ በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ሊሰፍን እንደማይችል መገንዘብ ይገባል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ የቀይ ባህር ጥያቄ ትክክለኛ መሆኑንም ተናግረዋል።
የባህር በር ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ለአካባቢው ሰላምና ለቀይ ባህር አፋር ሕዝብ ተጠቃሚነት መረጋገጥ ወሳኝ እንደሆነም አንስተዋል።