ቀጥታ፡

የባህር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲሱ ተርሚናል ሰፊ የኢኮኖሚ ዕድል ይፈጥራል 

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 30/2018 (ኢዜአ) ፦የባህር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲሱ ተርሚናል የጎብኚዎችን ፍሰት በማሳደግ በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ሰፊ የኢኮኖሚ ዕድል ይፈጥራል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

የባህር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲሱ ተርሚናል  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተመርቋል።

​የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በዚሁ ወቅት፣ የባህር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲሱ ተርሚናል የጎብኚዎችን ፍሰት በማሳደግ በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ሰፊ የኢኮኖሚ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።


 

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በክልሉ በርካታ የልማት ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን፣ ከተሞች ለነዋሪዎቻቸው ምቹና ዓለም ዓቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን ከፍ ለማድረግ በጎንደር፣ በባህር ዳር፣ በወልዲያ፣ በደሴና በሌሎች ከተሞችም እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የክልሉን ሁለንተናዊ እድገት የሚያሳልጡና የቱሪዝም ልማቱን የሚያፋጥኑ እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ትስስርን የሚያጠናክሩ አውሮፕላን ማረፊያዎችን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል። 

​ባህር ዳር በጣና ሐይቅ፣ በባህላዊ ቅርሶችና በተፈጥሯዊ መስህቦች የበለጸገች በመሆኗ፣ የአየር ትራንስፖርት አቅሟ መጠናከር የጎብኚዎችን ፍሰት በማሳደግ በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ሰፊ የኢኮኖሚ ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት።

በክልሉ በፌዴራል መንግስት ድጋፍ የቱሪዝም፣ የከተማ ልማትና የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች በስፋት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።


 

ክልሉን ተመራጭ የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እንደ ጎርጎራ ሪዞርት እና ጣና ሎጎ ሀይቅ ሪዞርት ያሉ ታላላቅ የቱሪስት የመዳረሻ ልማቶች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን አስታውሰዋል።   

የባህር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲሱ ተርሚናልም እነዚህን የልማት ሥራዎች በመደገፍ ለከተማዋ የቱሪዝም፣ የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የኮንፍረንስ ቱሪዝም እድገት አዲስ አቅም በመፍጠር የክልሉን ተወዳዳሪነት ያጠናክራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፣ የባህር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲሱ ተርሚናል በዘመናዊ የአየር ማረፊያ ደረጃዎች መሠረት መገንባቱን አስታውቀዋል።


 

የተሻለ የተሳፋሪ አገልግሎት በመስጠትም የከተማዋን የአየር ትራንስፖርት ተደራሽነት እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።

​የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሀገሪቱ የአየር ትራንስፖርት መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት እያከናወነ ያለው ተግባር ከተሞችን ከኢኮኖሚ፣ ከንግድና ከቱሪዝም ዕድሎች ጋር በተሻለ ለማገናኘት ያለመ ነው ብለዋል።

​አዲሱ ተርሚናል ባህር ዳርን በአየር ትራንስፖርት የበለጠ ተደራሽ በማድረግ የቱሪዝም እድገትን፣ የንግድ እንቅስቃሴን፣ የኢንቨስትመንት መስፋፋትንና የሥራ ዕድል ፈጠራን በማጠናከር ለከተማዋና ለአካባቢው ኢኮኖሚ ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት በመርሃ ግብሩ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም