ቀጥታ፡

በባሕር ዳር ከተማ የተከናወኑ አበረታች የልማት እንቅስቃሴዎች የብልፅግና አቅጣጫዎችን በግልጽ ያመላከቱ ናቸው 

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 30/2018 (ኢዜአ) ፦በባሕር ዳር ከተማ የተከናወኑ አበረታች የልማት እንቅስቃሴዎች የብልፅግና አቅጣጫዎችን በግልጽ ያመላከቱ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡  

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በባህር ዳር ከተማ የደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተርሚናል ዛሬ መርቀው ከፍተዋል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በባህር ዳር እና አካባቢዋ መልካም የልማት ጅምሮች መኖራቸውን መናገር ይቻላል ብለዋል፡፡

በቅርብ ጊዜ ውስጥ የጎርጎራ ሪዞርት እና በባህር ዳር ከተማ ውስጥ የሚገኘው "ፈለገ ጊዮን" ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል ብለዋል ።

ሁለቱን ታሪካዊና የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች ማገናኘት የሚችሉ በርካታ መርከቦች፤ በተለይም በኢትዮጵያ ትልቁ የሆነው "ጣና ነሽ" የተሰኘችው መርከብ ወደ አካባቢው እንድትመጣ መደረጉን አመልክተዋል።

ባህር ዳር በቱሪዝም ዘርፍ ለሀገሪቷ ማበርከት የምትችለው በርካታ የታሪክና የተፈጥሮ ሀብት እንዳላት አመልክተው፤ ይህ ሁሉ ጥረትና ኢንቨስትመንት ሊደረግ መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

በባሕር ዳር ከተማ ከመንግሥት ባሻገር በግል ባለሀብቶች ተሳትፎ በርካታ የቱሪዝም ዘርፍ ልማቶች ተጠናቅቀው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውንም ገልጸው፤ ሌሎችም በቅርቡ የሚጠናቀቁ መሆኑንም አብራርተዋል።


 

እነዚህ አበረታች ሥራዎች የከተማዋን የቱሪዝም ዘርፍ ከማነቃቃታቸውም በላይ ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ በከተማዋ የተከናወኑ የልማት አቅጣጫዎችን የሚያመላክቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከለውጥ በኋላ ባህር ዳር ከቱሪዝም በተጨማሪ በኢንዱስትሪ ከፍተኛ የእድገት አቅም እንዳላት አመልክተው፤ ይህንንም ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚ ለመቀየር ትልቅ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ተገንብቶ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸዋል፡፡

በሀገር እና በአህጉር ደረጃ ግዙፍ የሆነ ድልድይ የተገነባ መሆኑን ጠቁመው፤ ከተማዋን የበለጠ ውብና የኢኮኖሚ ማዕከል የሚያደርግ የኮሪደር ልማት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ግንባታው ሲጠናቀቅ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ እንግዶችን የሚያስተናግድ ስታዲየም እየተገነባ መሆኑን አመልክተዋል።


 

ከቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ቀጥሎ በኢትዮጵያ ሁለተኛው ትልቅ ተርሚናል በባህር ዳር መገንባቱ ለከተማዋ፣ ለክልሉ እና ለሀገሪቷ ትልቅ እሴት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በከተማዋ የተገነባው ዘመናዊ ኤርፖርት ተርሚናል ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የልማት አቅሟ በጥረትና በትጋት ልቆ እንዲታይ ማድረግ እንደሚቻል የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንንም ወደ ተጨባጭ ውጤት ለመቀየር የህብረተሰቡ ትብብር ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡


 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተከናወነውን ሪፎርም አድንቀው፤ ፕሬዝዳንቱ ከቢሯቸው ሆነው የክልሉን ችሎቶች በቨርቹዋል ለመከታተልና ቅሬታ ለማዳመጥ የሚያስችል አሰራር በመዘርጋታቸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም