ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል በክረምት የበጎ ፈቃድ መርሐግብር ነፃ የህክምና አገልግሎት እየተሰጠ ነው

መቱ ፤ ሐምሌ 30/2018 (ኢዜአ) ፦ በኦሮሚያ ክልል በክረምት የበጎ ፈቃድ መርሐግብር ነፃ የህክምና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የኦሮሚያ ጤና ቢሮ በኢሉባቦር ዞን እና በመቱ ከተማ የሚገኙ የመንግሥትና የግል የጤና ተቋማትን በማሳተፍ ያዘጋጀውን የተቀናጀ የበጎ ፈቃድ የጤና አገልግሎት መርሃ ግብር በመቱ ከተማ በይፋ አስጀምሯል።

የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሲስተር ትዕግስት ተፈሪ በወቅቱ እንደገለጹት፤ በክልሉ በክረምት የበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴ በአቅም አለመኖር ምክንያት ህክምና ማግኘት ላልቻሉ ወገኖች በነፃ አገልግሎት እየተሰጠ ነው።


 

ይህም ሀብትንና ጊዜን በመቆጠብ ተደራሽነትን ከማስፋት ባሻገር፣ ጤናማ ማኅበረሰብን በማፍራት ዜጎች በልማቱ ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማስቻል ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

አገልግሎቱ ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በመከላከል ላይ ያተኮሩ የቅድመ ምርመራና የሕክምና ተግባራትን ያካተተ መሆኑንም ሲስተር ትዕግስት ጠቁመዋል።

በዚሁ መሠረት የዓይን፣ የስኳር፣ የደም ግፊት፣ የጡትና የማኅጸን ጫፍ ካንሰር ቅድመ ምርመራዎች፤ የሕፃናትና ነፍሰ ጡር ሴቶች እንዲሁም የምግብ እጥረት ምርመራና ሕክምና አገልግሎቶች በስፋት እንደሚከናወኑም ጠቅሰዋል።

የኢሉባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ በበኩላቸው፤ በዞኑ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተከናወኑ በሚገኙ ተግባራት ዘርፈ ብዙ ችግሮች እየተቀረፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

በጤናው ዘርፍ በሚከናወነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም ተመሳሳይ ተልዕኮ ያላቸው ተቋማት የጋራ አቅማቸውን በማጠናከር የሕብረተሰቡን ማኅበራዊ ችግሮች ለመፍታት ጥረት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

የመቱ ከተማ ከንቲባ አቶ ተሻለ ኤጄርሶ በበኩላቸው፤ በሁሉም መስኮች እየተተገበሩ የሚገኙት የበጎ ፈቃድ ተግባራት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት እያገዙ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

በጎ ፈቃድ አገልግሎቱ መስጠትንና ለሌላው መትረፍን ባህል ያደረገ ትውልድ ከመገንባትና ወንድማማችነትን ከማጠናከር አኳያም ትልቅ አቅም እየሆነ መምጣቱን አመልክተዋል።

ከአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መካከል ወይዘሮ ኢየሩሳሌም ተመስገን፣ የስኳርና የደም ግፊት በሽታዎች ቅድመ ምርመራ አገልግሎትን በነፃ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በተደረገላቸው ነፃ ምርመራና ሕክምና ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

ዛሬ ያገኙት የቅድመ ምርመራ አገልግሎት የጤና ሁኔታቸውን አስቀድመው በማወቅ ለወደፊቱ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ለማድረግ እንደሚያግዛቸው የተናገሩት ደግሞ አቶ ገበየሁ ተካ ናቸው።

በተለያዩ የጤና ችግሮች ውስጥ እያሉ በአቅም ማጣት ምክንያት ወደ ጤና ተቋማት ሄደው መታከም ያልቻሉ ዜጎች፣ በዚህ አጋጣሚ አስፈላጊውን ሕክምና እያገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም