ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል 47 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ ገብተዋል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 30/2018 (ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል 2018 በጀት ዓመት 47 አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ መግባታቸውን የክልሉ ኢንተርፕራይዝ ልማትና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ ወደ ስራ የገቡ ኢንዱስትሪዎች ለዜጎች የስራ እድል እየፈጠሩ መሆናቸውም ተገልጿል።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ ሃምዲ ሰለሃዲን እንደገለጹት በክልሉ በተለይም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም ከማጎልበት ባለፈ በዘርፉ መነቃቃት እንዲፈጥር እያስቻለ ነው።

ወደ ስራ የገቡት ኢንዱስትሪዎች ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶችን በማጎልበትና ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጪ ምንዛሬን እያስቀሩና ለኢኮኖሚው ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያበረከቱ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

በተጠናቀቀው 2018 በጀት ዓመት 47 መካከለኛ እና አነስተኛ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንደገቡ ገልጸው፣ ተጨማሪ 16 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ደግሞ የግንባታ ሥራቸውን አጠናቀው ወደ ማሽነሪ ተከላ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

ሥራ የጀመሩ ኢንዱስትሪዎችም ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጪ ምንዛሬን ከማስቀረት አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያበረከቱ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

አምራች ኢንዱስትሪዎቹ ከሃይል አቅርቦትና ከመሰረተ ልማት ጋር በተያያዘ ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት መሰራቱን ገልጸው  ዘንድሮ  በኢንዱስትሪ ዘርፉ ብቻ 3 ሺህ 935 ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል ተፈጥሯል ብለዋል።

በቀጣይም የኢንዱስትሪ ዘርፍ የማጎልበት ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉም አቶ ሀምዲ ገልጸዋል።

በፋብሪካዎቹ የስራ እድል የተፈጠረላቸው ወጣቶችም እራሳችውንና ቤተሰባቸውን ከመደጎም ባለፈ ልምድ እየቀሰሙና በትርፍ ጊዜያቸውም የኮሌጅ ትምህርት እንዲከታተሉ እድል እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

በሐረሪ ክልል 196 ከፍተኛ፣ መካከለኛና አነስተኛ አምራች ኢንዳስትሪዎች በማምረት ስራ ላይ እንደሚገኙም ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም