ቀጥታ፡

እናቶች ልጆቻቸውን ጡት በማጥባት ጤናማና አምራች ዜጋ ማፍራት ይጠበቅባቸዋል

ባህርዳር ፤ ሐምሌ 30/2018 (ኢዜአ) ፦እናቶች ልጆቻቸውን ጡት በማጥባት ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር እንዲችሉ የተቀናጀ የግንዛቤ ፈጠራ ስራን በትኩረት መስራት እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ክልላዊ አለም አቀፍ የጡት ማጥባት ሳምንት "ጡት ማጥባት ለዘላቂ ህይወት ጅማሮ" በሚል መሪ ቃል በባህር ዳር ከተማ ዛሬ ታስቦ ውሏል።

በጤና ሚኒስቴር የመከላከል ተኮር ስርዓተ ምግብ አስተባባሪ አቶ መርሻ ወርቁ በመድረኩ እንደገለጹት፣ እናቶች ህጻናትን ለስድስት ወራት ጡት ብቻ በመመገብ  የመቀንጨር ችግርን ማቃለል አለባቸው።


 

በተለይ  ከተወለዱ ጊዜ ጀምሮ ለስድስት ወራት ያለምንም ተጨማሪ ምግብ የእናታቸውን ጡት መመገብ እንዲሁም እስከ ሁለት ዓመትም ከተጨማሪ ምግብ ጋር ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።

ይህም ህጻናት በሽታዎችን በመቋቋም የተመጣጠነ እድገት እንዲኖራቸውና ጤናማ እንዲሆኑ በማስቻል በአካልና በአዕምሮ የዳበረ አምራች ዜጋ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ነው የተናገሩት።

እናቶች ለልጆቻቸው የዱቄት ወተትን ከመጠቀም ይልቅ ንጽህናው የተጠበቀውን የጡት ወተትን በመመገብ ልጆቻቸውን ለበሽታ እንዳይጋለጡ ማድረግ እንዳለባቸው መክረዋል።

የዛሬው በአል ዋና አላማም እናቶች ልጆቻቸውን በአግባቡ ጡት አጥብተው ማሳደግ እንዲችሉ ግንዛቤ ለመፍጠርና የህክምና ባለሙያዎችና ፖሊሲ አውጪዎችም ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የስርዓተ ምግብ አስተባባሪ አቶ ስሜነህ ወርቁ በበኩለቸው፣ በክልሉ በሚስተዋለው የግንዛቤ ክፍተት ምክንያት በርካታ ህጻናት የመቀንጨር ችግር ይታይባቸዋል። 

በክልሉ የሚገኙ ህጻናት የሚያስፈልጋቸውን የእናት ጡት በአግባቡ ካላገኙ ከሚጠበቅባቸው ክብደት በታች እንደሚሆኑ አስረድተዋል።

ዛሬ የተካሄደው መድረክ ዋና አላማም እናቶች ልጆቻቸውን ጡት እንዲያጠቡ ለማበረታታትና ለመደገፍ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

በዛሬው እለት በባህርዳር ከተማ በተካሄደው መድረክም የክልልና የፌዴራል የዘርፉ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም