ቀጥታ፡

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የሚያስችል አቅም እየተገነባ ነው

ሀዋሳ ፤ ሐምሌ 30/2018 (ኢዜአ) ፦በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥና ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት የሚያስችል አቅም እየተገነባ መሆኑን የውሀና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

የሚኒስቴሩ እና የተጠሪ ተቋማቱ አመራሮች የአረንጓዴ አሻራና የበጎ አድራጎት መርሃ ግብርን በሲዳማ ክልል ሰሜናዊ ሲዳማ ዞን በሸበዲኖ ወረዳ አካሄደዋል።


 

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥና ሀገራዊ ግቦችን ለማሳካት የሚያስችል አቅም እየተገነባ ነው።

በየዓመቱ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እየተተከለ ያለው ችግኝ የአካባቢ መራቆትና የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ፣ የውሃ ምንጮችን በማጎልበት የውሃ ሀብት መጠንን ያሳደገ መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዛሬውም መርሃ ግብር የዚሁ አካል እንደሆነ ጠቁመዋል።


 

ከችግኝ ተከላው ጎን ለጎንም በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሚኒስቴሩ አጋዥ የሌላቸው ወገኖችን በመደገፍ አጋርነቱን እያሳየ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዛሬው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሚኒስቴሩ በሸበዲኖ ወረዳ ዲላ አፈራራ ቀበሌ የሰባት አቅመ ደካማ ወገኖችን ቤት አፍርሶ ለመገንባት መረከቡንና ቤቶቹ ደረጃቸውን ጠብቀው ተገንብተው በአጭር ጊዜ ውስጥ ርክክብ እንደሚደረግም ገልጸዋል።

የሲዳማ ክልል ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ከበደ ጋኖሌ በበኩላቸው፤ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባለፉት አምስት ዓመታት በመጠጥ ውሃና ኢነርጂ አቅርቦት ረገድ በክልሉ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል ብለዋል።


 

በዚህም የክልሉ የመጠጥ ውሃ ሽፋን ወደ 75 በመቶ ማደጉንና በኢነርጂው ዘርፍ እየገነባቸው ካሉ አምስት ፕሮጀክቶች ሁለቱ ተመርቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ገልጸዋል።

በሚኒስቴሩ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ የውብዳር አሚኖ፤ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ በአካባቢው የገጽና ከርሰ ምድር ውሃን በማጎልበት ውሃ ፍለጋ ረጅም ርቀት የሚጓዙ እናቶችን ድካም አስቀርቷል ብለዋል።

የሰሜን ሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፃዲቁ ባጢሶ፤ ሚኒስቴሩ በመጠጥ ውሃ አቅርቦትና በኢነርጂው ዘርፍ እያከናወነ ያለው ተግባር በዞኑ በርካቶችን ተጠቃሚ ማድረጉን ጠቁመው፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎትና በችግኝ ተከላው እያበረከተ ላለው አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።


 

በሸበዲኖ ወረዳ የዲላ አፈራራ ቀበሌ ነዋሪው አቶ አበራ ካሼራ ቤታቸው በመፍረሱ በክረምት ዝናብና ብርድ ሲፈተኑ መቆየታቸውን ገልጸው አሁን ቤታቸውን ሊታደስላቸው በመሆኑ መደሰታቸውን ተናግረዋል።


 

በመርሃ ግብሩ ለ500 ተማሪዎች የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገላቸው ሲሆን፣ የሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማቱ ሠራተኞች የፍራፍሬና ሌሎች ሀገር በቀል ችግኞችን ተክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም