ፓርኩን በማልማትና በመጠበቅ ዘላቂ የገቢ ምንጭ ለማድረግ ቅንጅታዊ ሥራን ማጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ፓርኩን በማልማትና በመጠበቅ ዘላቂ የገቢ ምንጭ ለማድረግ ቅንጅታዊ ሥራን ማጠናከር ይገባል
ሮቤ ፤ ሐምሌ 30/2018 (ኢዜአ) ፦የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን በማልማትና በመጠበቅ ዘላቂ የገቢ ምንጭ ለማድረግ በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳትና ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ።
በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገበው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከ2019 አስከ 2029 ዓ.ም የሚተዳደርብት የአስር ዓመት ማኔጅመንት ፕላን ላይ የሚመክር አውደ ጥናት በባሌ ሮቤ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ እንደገለጹት፤ ልቅ ግጦሽ፣ የደን ጭፍጨፋና ሕገወጥ ሰፈራ የፓርኮችን ህልውና ሲፈታተኑ ከነበሩት ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
ባለፉት ዓመታት በብሔራዊ ፓርኮችና ጥብቅ አካባቢዎች በቅንጅት በተሰሩ ሥራዎች ፓርኮችን የሚፈታተኑ ተግዳሮቶች እየቀነሱ መጥተዋል።
በተለይ የፌደራል፣ የክልልና የፓርኮች አካባቢ አስተዳደሮች ከማኅበረሰቡ ጋር በመሆን ባደረጉት የተቀናጀ ጥረት በፓርኮች ላይ ሲደርሱ የነበሩ እነዚህ ችግሮች መቀነሳቸውን ነው ያስረዱት።
ባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን በማልማትና በመጠበቅ ዘላቂ የገቢ ምንጭ ለማድረግ በቅንጅት መሥራት እንደሚገባም ዳይሬክተሩ አቶ ኩመራ አስገንዝበዋል።
ፓርኩን በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የዞኑ አመራሮችና ነዋሪዎች ድርሻ ከፍተኛና ታሪካዊ እንደነበርም አስታውሰዋል።
ብሔራዊ ፓርኩ በዓለም ቅርስነት ከተመዘገበ በኋላም በውስጡ ሰፍረው ለነበሩ ነዋሪዎች አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎ ወደ ሌላ አካባቢ እንዲዘዋወሩ መደረጉ ትልቅ ውሳኔ የሚጠይቅ በመሆኑ የዞኑን አስተዳደር አመስግነዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት ፓርኩ በቀጣይ የሚተዳደርበት የአስር ዓመት ማኔጅመንት ፕላን በዘርፉ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ በጎ ተግባራትን በማስቀጠል ፓርኩን የተሻለ ደረጃ ላይ የማድረስ ግብ አለው።
የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሃኪም አልይ በበኩላቸው እንዳሉት፣ አስተዳደሩ ብሔራዊ ፓርኩንና በውስጡ ያለውን ብዝኃ ህይወት በአግባቡ እንዲጠበቅ በትኩረት እየሰራ ነው።
የፕላኑ ዋና ዓላማም ፓርኩን በመጠበቅና በማልማት የአካባቢውን ማኅበረሰብ ዘላቂ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መሆኑን ተናግረዋል።
አስተዳደሩ ፓርኩን ለማልማትና ለመጠበቅ በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር መስራቱን በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ለውይይት የቀረበው የአስር ዓመት ማኔጅመንት ፕላን ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ የተዘጋጀ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊ አቶ ሻሚል ከድር ናቸው።
ፕላኑ ተግዳሮቶችን ለይቶ በመፍታት ፓርኩን ለመጠበቅና ለዘላቂ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለማዋል እንደሚያስችል ተናግረዋል።
ፕላኑም በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት በቱሪዝም ልማት ዘርፍ፣ በመሰረተ ልማትና በስነ-ምህዳር ጥበቃና አመራር ረገድ ለመድረስ የታቀደውን ዝርዝር ተግባር ማካተቱን አቶ ሻሚል ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ካስመዘገበቻቸው ዓለም አቀፍ ቅርሶች መካከል አንዱ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ነው።
ፓርኩ የደጋ አጋዘንና ቀይ ቀበሮን ጨምሮ የበርካታ ዱር እንስሳት፣ አዕዋፋትና ዕፅዋት መኖሪያም እንደሆነ ይታወቃል።