የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ ባለፈ ለአፍሪካ የሚተርፍ የአየር ኃይል አቅም ተገንብቷል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ ባለፈ ለአፍሪካ የሚተርፍ የአየር ኃይል አቅም ተገንብቷል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 30/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ ባለፈ ለአፍሪካ የሚተርፍ የአየር ኃይል አቅም መገንባቱን የኢትዮጵያ አየር ኃይል ምክትል አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል መሰረት ጌታቸው ገለጹ።
በቤኒን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና ኢኖቬሽን ሚኒስትር ማሁና አክፕሎጋን የተመራ ቡድን በቢሾፍቱ የኢትዮጵያን አየር ኃይል ጎብኝቷል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳና ምክትል አዛዡ ብርጋዴር ጄኔራል መሰረት ጌታቸው የአየር ኃይልን የጥገናና የማምረት አቅም በተመለከተ ገለፃ አድርገውላቸዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ምክትል አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል መሰረት ጌታቸው በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የቤኒን የልዑካን ቡድን በአየር ኃይሉ የጥገናና የቴክኖሎጂ እንዲሁም የማምረት አቅም ተደንቀዋል።
በኢትዮጵያ እና ቤኒን አየር ኃይሎች መካከል ትብብር መፍጠር የሚያስችል የሚፈልጉት የቴክኖሎጂና የስልጠና አቅም እንዳለም አረጋግጠውልናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል በአፍሪካ ካሉ ትልልቅ የአቬዬሽን ኢንዱስትሪዎች አንዱ መሆኑን በመጥቀስ፤ በዕውቀት በቴክኖሎጂና ራስን በመቻል አቅም ልቆ መገኘቱን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ አየር ኃይል የጥገና፣ የሰው አልባ አውሮፕላን ምርት፣ የመለዋወጫና ሌሎች የማምረቻ ፋብሪካዎች አቅም በፍጥነት ማደጉን ገልጸው፤ ጉብኝት የሚያደርጉ የአፍሪካ ሀገራትም የሚያዩት አቅም ከጠበቁት በላይ እንደሚሆንባቸው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል የማድረግ አቅም እያደገ በመምጣቱ ባለፉት ሶስት ወራት ከአራት የአፍሪካ ሀገራት ጋር የትብብር ስምምነት መፈራረሙንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚመጥን አየር ኃይል መገንባት እንደሚቻል የተረዳነው ዐይናችንን የገለጥነው ከሪፎርሙ በኋላ ነው ሲሉም አስታውቀዋል።
ተቋሙ ቴክኖሎጂ እንዲታጠቅና እንዲያለማ፣ ሀብቱን በአግባቡ እንዲጠቀም በማድረግ ብዙ ሀብት እንዲያፈራ የማይገለጹ አቅሞችን እንዲገነባ የተደረገው በሪፎርሙ መሆኑን ገልጸዋል።
የአየር ኃይሉ አሰራሩን ወደ ዲጂታል በመቀየር ለአፍሪካ የሚተርፍ አቅም መገንባቱን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ህንድ ውቅያኖስ ይደርሳል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሚታይ የሚጨበጥ ለውጥ ማምጣቱን ጠቁመው፤ የሌሎች ሀገራትን ፍላጎትም ታሳቢ ያደረገ የማምረት አቅም ገንብቷል ብለዋል።
ከአምናው ዘንድሮ የማምረት አቅማችን ጨምሯል ያሉት ምክትል አዛዡ፤ አንዳንድ መለዋወጫዎችን በቀን እስከ ሶስት ሺህ 500 የማምረት አቅም መገንባቱን ገልጸዋል።