ቀጥታ፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ለማደናቀፍ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ መንግሥት የማያዳግም እርምጃ መውሰዱን አጠናክሮ ይቀጥላል 

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 30/2018 (ኢዜአ) ፦በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ለማደናቀፍ በሚንቀሳቀሱና የሀገር ሀብት በሚመዘብሩ አካላት ላይ መንግሥት የማያዳግም እርምጃ መውሰዱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ ገለጹ።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ በሙስና፣ በብልሹ አሰራር እና በህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች ላይ የተወሰዱ እርምጃዎችን አስመለክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

መንግሥት ከህዝብ የቀረቡለትን ጥቆማዎች እና አቤቱታዎች መነሻ በማድረግ በልዩ ልዩ የአገልግሎት መስጫ ማዕቀፎች እና የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ያካሄዳቸውን ጥልቅ ፍተሻዎች፣ የምርመራ ውጤቶች እና የተወሰዱ የህግ ተጠያቂነት እርምጃዎችን አስመልክተው ነው ዝርዝር መግለጫ የሰጡት፡፡ 

በመግለጫቸው እንደጠቆሙት፤ የመደመር መንግሥት ያልተገባ ሀብት እና ጥቅም የመፈለግ አዝማሚያዎችን የሀገር እድገት አደጋ አድርጎ በመውሰድ ገና ከጠዋቱ ቀይ መስመር በማስመር ህጋዊ እና ተቋማዊ ሪፎርሞችን ሲያካሂድ ቆይቷል ብለዋል። 

ይህ መረጃ በብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት፣ በፌደራል ፖሊስ እና በኢፌዴሪ ፍትህ ሚኒስቴር በጋራ የተቀናጀ ስልታዊ ጥናት፣ ክትትል እና ህጋዊ ፍተሻ የተገኘ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።  

እነዚህ እርምጃዎች ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችውን የብዙሃን ዘርፍ ማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም እና የህዝቦቿን ህይወት የመቀየር ሂደት ከሚያጋጥሙ እንቅፋቶች ለመጠበቅ ያለሙ ናቸው ብለዋል። 

በዚህም በትልቁ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ላይ አደጋ ለመፍጠር፣ ምርቶችን በመጋዘን በመሸሸግ እና በመደበቅ የምርት እጥረት እንዲከሰት ያደረጉ፣ በኮንትሮባንድ ንግድ የተሰማሩ እና የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ በመፍጠር በህብረተሰቡ ላይ የኑሮ ጫና እና ምሬት እንዲፈጠር ያደረጉ አካላት ላይ ሰፊ ኦፕሬሽን መካሄዱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ከ7 ሺህ በላይ የሚሆኑ የንግድ ተቋማት፣ ሱቆች እና መጋዘኖች በህግ እርምጃ ተወስዶባቸዋል፤ እንዲዘጉም ተደርገዋል ብለዋል።  

ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን በመቀመር፣ በጥቁር ገበያ እና በህገ-ወጥ ሐዋላ በመሰማራት፣ እንዲሁም ነጋዴዎች ከባንክ ማግኘት የሚገባቸውን የውጭ ምንዛሬ እንዳያገኙ እንቅፋት በሆኑ አካላት ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል፡፡ 

የውጭ ምንዛሬን በስውር በማንቀሳቀስ እና ጥቁር ገበያን በማስፋፋት የተጠረጠሩ 169 ግለሰቦች እና የንግድ ተቋማት በህግ አግባብ ተጠያቂ ሆነዋል ብለዋል። 

በተጨማሪም በፋይናንስ ተቋማት፣ ኤቲኤም ማሽኖች እና በግለሰቦች አካውንት ላይ የሳይበር ማጭበርበር የፈጸሙ እና ያለፈቃድ የክሪፕቶ ከረንሲ መተግበሪያዎችን ሲጠቀሙ የነበሩ ተቋማት በህግ እንዲጠየቁ ተደርጓል ብለዋል።

በሌላ በኩል፣ ያለፈቃድ በመንቀሳቀስ በማህበረሰቡ እና በወጣቶች ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ቀውስ ያመጡ፣ ግብር የሚሸሹ 36 ህገ-ወጥ የቤቲንግ ድርጅቶች እና በበየነ መረብ የሚሰሩ ተቋማት እንዲዘጉ እና በህግ እንዲጠየቁ ተደርጓል ብለዋል።

ከሀገሪቱ አምስት የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ በሆነው የማዕድን ዘርፍ በተለይም በወርቅ ምርት ላይ የሚከናወነውን የኮንትሮባንድ ዝውውር እና ድለላ ለማስቆም በተደረገ ተደራጅቶ የመስራት ምርመራ፣ ምርቱን ወደ ብሔራዊ ባንክ ከማስገባት ይልቅ ለማሸሽ የሞከሩ አምራቾች፣ አዘዋዋሪዎች እና ደላሎችን ጨምሮ 138 ግለሰቦች በህግ ቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል።

መንግሥት ህዝቡን ከጫና ለመጠበቅ ከፍተኛ በጀት በሚመድብበት የነዳጅ አቅርቦት ላይ የሎጂስቲክስ እና የስርጭት አሻጥር በመፍጠር፣ ነዳጅን ወደ ጎረቤት ሀገራት በማሸሽ፣ መጋዘን ውስጥ በመደበቅ እና ኮታን ለግል ጥቅም በማዋል የቀውስ አዝማሚያ የፈጠሩ አካላት ተለይተዋል። 

በዚህ የተደራጀ ጥቅም ትስስር ውስጥ የተሳተፉ የመንግሥት አካላት፣ ነጋዴዎች እና የሎጂስቲክስ ባለሙያዎች በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፣ ስርዓቱን ከሙስና የጸዳ ለማድረግ ጥብቅ መመሪያ ወጥቷል ብለዋል።

አርሶ አደሩ ግብአቱን በወቅቱ እንዳያገኝ ያደረጉ፣ የኮንትራክተሮች እና የደላሎች አሻጥር ያለበት የተጋነነ ዋጋ ያለው ግዢ እንዲፈጸም ያደረጉ እና ግዢው እንዲጓተት ያደረጉ አካላት በጥልቀት ተመርምረዋል ብለዋል። 

በዚህም ድርጊት የተሳተፉ ከፍተኛ አመራሮች፣ ደላሎች እና ግለሰቦች በህግ አግባብ ተጠያቂ ሆነዋል።

በተቋሙ የፕሮጀክት ስራዎች ላይ የተጋነነ ዋጋ በመጠየቅ፣ የኃይል መሰረተ ልማት ግንባታዎች እንዲጓተቱ በመመሣጠር ሀገር ላይ የኢኮኖሚ ጫና ለማሳደር የሞከሩ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የፕሮጀክት አስተባባሪዎች፣ ተባባሪ ኮንትራክተሮች እና ነጋዴዎች በጥናት ተደርሶባቸው ተጠያቂ እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል።

በስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ማዕቀፍ የሚከናወነውን ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ እና የዜጎችን ደህንነት የሚያዛቡ፣ ህጋዊ ውል ከሌላቸው ሀገራት ጋር አየር በአየር እና በህገ-ወጥ ኤጀንሲዎች ውል በማስመሰል ሲላኩ የነበሩ፣ 8 ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች፣ ኤጀንሲዎች እና ደላሎች በህግ ተጠያቂ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

በተጨማሪም በሊቢያ፣ በጅቡቲ እና በሞያሌ ድንበሮች በኩል በህገ-ወጥ መንገድ ዜጎችን ሲያሸሹ በነበሩ ደላሎች ላይ የተጀመረው ምርመራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።

በጉምሩክ እና ገቢዎች ዘርፍ የተዛባ የግብር ግምት በማድረግ፣ የታክስ ስወራ እንዲኖር በር በመክፈት፣ የገቢ እቃዎችን ዋጋ በመቀነስ እና ሀገሪቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠር የመንግሥት ገቢ እንድታጣ ከነጋዴዎች ጋር በመመሣጠር የሙስና መረብ የዘረጉ ባለሙያዎች እና አመራሮች ላይ የማጥራት እና የህግ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።

መንግሥት አገልግሎቶችን በዲጂታል በማስደገፍ፣ አሰራሮችን በማዘመን እና ተጠያቂነትን በማስፈን የጀመረውን የተቀናጀ ፀረ-ሙስና ትግል አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰዋል።  

ህዝቡም ጥቆማዎችን በመስጠት እና ከጸጥታና ፍትህ ተቋማት ጎን በመቆም የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም