ከምክክር ጉባኤው የሚወጡ ውሳኔዎች የተሻለች ሀገርን ለተተኪው ትውልድ ለማስረከብ ያስችላሉ - ኢዜአ አማርኛ
ከምክክር ጉባኤው የሚወጡ ውሳኔዎች የተሻለች ሀገርን ለተተኪው ትውልድ ለማስረከብ ያስችላሉ
ሆሳዕና ፤ ሐምሌ 30/2018 (ኢዜአ) ፦ ከምክክር ጉባኤው የሚወጡ ውሳኔዎች ለዘመናት የቆዩ ስብራቶችን በመጠገን የተሻለች ሀገርን ለተተኪው ትውልድ ለማስረከብ እንደሚያስችሉ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የባህል ሽማግሌዎች ገለፁ።
የባህል ሽማግሌዎቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ ከምክክር ጉባኤው የሚወጡ ውሳኔዎች ለዘመናት የቆዩ ስብራቶችን በመጠገን የተሻለች ሀገርን ለተተኪው ትውልድ ለማስረከብ እንደሚያስችሉ ገልጸዋል።
የሀዲያ የባህል ሽማግሌ ዳኛ ብርሃኑ ጡሞሮ፣ የምክክር ሂደቱ የልዩነት እሳቤዎችንና ጎታች አመለካከቶችን በመቅረፍ ረገድ ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል።
ጉባኤው የተሻለች ሀገርን ለተተኪው ትውልድ ለማስረከብ የሚረዱ ውሳኔዎች የሚቀመጡበት መሆኑን ተከትሎ ወቅቱን በተስፋ እየተጠባበቁ እንደሚገኙም ነው ያስረዱት።
ከምክክር ጉባኤው የሚወጡ ውሳኔዎች ኢትዮጵያ የተደመረ አቅሟንና የውስጥ ጸጋዎቿን በማስተባበር ሁለንተናዊ ዕድገቷን እንድታረጋግጥ እንደሚያስችላት ተናግረዋል።
የስልጤ ባህል ሽማግሌ ሼህ ሙዘይን ሰይድ በበኩላቸው፤ አለመግባባቶችን በመፍታት በአብሮነት ለመጓዝ የምክክር ሂደቱ ፍቱን መፍትሔ እንደሚያመጣ ተናግረዋል።
በምክክሩ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ተመካካሪዎች ከመላ ሀገሪቱ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ በመሆኑ ሙሉ ውክልና እንዳላቸው አመልክተዋል።
እየተካሄደ ከሚገኘው የምክክር ጉባኤ በዜጎች መካከል ለልዩነት መንስኤ ሆነው የቆዩ ስብራቶችን በመጠገንና አብሮነታትን ለማጠናከር የሚያስችሉ ውሳኔዎችን እንደሚጠብቁም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በመደመር መንግሥት እየተመዘገቡ የሚገኙ ስኬቶችን ይበልጥ ለማጠናከር የኢትዮጵያውያን በቅንጅት መጓዝ ቀዳሚው አማራጭ ነው ያሉት ደግሞ የጠምባሮ የባህል ሽማግሌ ታሪኩ በርገኖ ናቸው።
ለዚህም ስኬት ያደሩ ችግሮችን በመፍታት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በጠረጴዛ ዙሪያ በምክክር የጋራ ተግባቦት መፍጠር ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።