ሲዳማ ቡና እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ተጋጣሚዎቻቸውን አውቀዋል - ኢዜአ አማርኛ
ሲዳማ ቡና እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ተጋጣሚዎቻቸውን አውቀዋል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 30/2018 (ኢዜአ)፦ የ2026/27 የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ እና የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ የዕጣ ማውጣት ስነ ስርዓት ዛሬ በግብጽ ካይሮ ተካሄዷል።
በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የሚሳተፈው ሲዳማ ቡና ከቻዱ ክለብ ኤግሎንስ ጋር ይጫወታል።
ሲዳማ ቡና በደርሶ መልስ ውጤት ድል ከቀናው በቀጣዩ ዙር ከቡሩንዲው ኤግሌ ኖይር እና ከሱዳኑ አል ሂላል አሸናፊ ጋር የሚጫወት ይሆናል።
የ2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ሲዳማ ቡና በአህጉራዊ መድረክ ሲሳተፍ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከሱዳኑ አል ሂላል አልሳሂል ጋር ጨዋታውን ያደርጋል።
ወልዋሎ ወደ ቀጣዩ ዙር ካለፈ ከዛንዚባሩ ኬኤምኬኤም እና ከሊቢያው አል አህሊ ትሪፖሊ አሸናፊ ጋር የሚጫወት ይሆናል።
የዘንድሮው የኢትዮጵያ ዋንጫ ባለቤት ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በአህጉራዊ መድረክ ሲሳተፍ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ሲዳማ ቡና እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጨዋታቸውን በነሐሴ 2018 ዓ.ም እና መስከረም 2019 ዓ.ም ያከናውናሉ።