የትራፊክ አደጋን ከመከላከል ጎን ለጎን በአደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች በደም ልገሳ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የትራፊክ አደጋን ከመከላከል ጎን ለጎን በአደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች በደም ልገሳ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው
አዳማ ፤ ሐምሌ 30/2018 (ኢዜአ) ፦ የትራፊክ አደጋን ከመከላከል ጎን ለጎን በአደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች በደም ልገሳ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በቅንጅት እየሰራ መሆኑን በኦሮሚያ ክልል የአዳማ ከተማ መንገድ ትራንስፖርት ኤጀንሲ አሰታወቀ።
ኤጀንሲው ከአዳማ ደም ባንክና ከከተማዋ ትራፊክ ፖሊስ ጋር በመተባበር ''በትራፊክ አደጋ ለተጎዱ ሰዎች ደም እንለግስ'' በሚል መሪ ሐሳብ ያዘጋጀው የደም ልገሳ መርሃ ግብር ተካሄዷል።
በወቅቱም የአዳማ ከተማ መንገድ ትራንስፖርት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ መኩሪያ ሹሚ እንዳስታወቁት፤ የደም ልገሳ መርሃ ግብሩ ኤጀንሲው እያካሄደው ያለው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አካል ነው።
ኤጀንሲው በዋናነት የትራፊክ አደጋን ለመከላከል ለተለያዩ አካላት ግንዛቤ ከማስጨበጥ ባለፈ፣ በትራፊክ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች በደም ልገሳ ለመድረስ የትራንስፖርት ተዋናዮችን በማስተባበር እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ለ5ኛ ጊዜ በአዳማ መናኸሪያ በተዘጋጀው በዚሁ መርሃ ግብር ላይ 150 ዩኒት ደም ለማሰባሰብ መታቀዱን ገልጸዋል።
እሳቸውም ደም መለገሳቸውን ጠቁመው፤ ደም መለገስ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት መታደግ በመሆኑ የሕሊና እርካታ የሚሰጥ ነው ብለዋል።
የአዳማ ደም ባንክ ኃላፊ አቶ ከተማ ደቀባ በበኩላቸው፤ በተሽከርካሪ አደጋ ለተጎዱ ሰዎች ድንገተኛ ሕክምና መስጠት የሚቻለው በቂ ደም ሲገኝ በመሆኑ ሁላችንም ደም መለገስን ባህል ልናደርግ ይገባል ነው ያሉት።
ደም በመለገስ የወገንን ሕይወት መታደግ ሰብዓዊ አገልግሎት በመሆኑ ሕብረተሰቡ ይህን ተግባር ሊደግፍ ይገባል ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ደም ከለገሱት መካከል በአዳማ ደምበላ ክፍለ ከተማ የትራፊክ ግንዛቤና ደኅንነት ክትትል ኃላፊ ኢንስፔክተር እሸቱ መሸሻ ለ15ኛ ጊዜ ደም መለገሳቸውን ገልጸዋል።
በዚህም በትራፊክ አደጋም ሆነ በወሊድ ወቅት የደም እጥረት ላጋጠማቸው ወገኖች በመድረሳቸው ደስታ እንደሚሰማቸውም ተናግረዋል።
ሌላኛዋ ደም ለጋሽ የባጃጅ ትራንስፖርት ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ሳዲያ አብዲሪያ በበኩሏ፤ ደም ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች በበጎ ፈቃደኝነት ደም መለገሷን ገልጻለች።
በቀጣይም በየሦስት ወሩ ደም ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ደሟን ለመለገስ ማቀዷን ገልጻለች።