የአቪዬሽን መሠረተ ልማት ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና ምሰሶ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአቪዬሽን መሠረተ ልማት ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና ምሰሶ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 30/2018 (ኢዜአ) ፦ የአቪዬሽን መሠረተ ልማት ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና ምሰሶ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ዛሬ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የባሕር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲስ የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል የአየር መንገዳችን ደማቅ የስኬት ጉዞ ማሳያ ነው ብለዋል።
ይህ ዘመናዊ ተርሚናል ለባሕር ዳርና ለአካባቢው ፈርጀ ብዙ ኢኮኖሚያው ፋይዳ ያለው ከመሆኑም በላይ፣ ከተማዋን ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቀጥሎ የሁለተኛው ትልቅ የዓለም አቀፍ አቪዬሽን ማዕከልነት ሚና እንዲኖራት የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ የላቀ ጥራትን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከፍተኛ የማስተናገድ አቅም እንዲኖረው ተደርጎ የተገነባው ይህ ደረጃውን የጠበቀ ተርሚናል፣ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ሀብቶችን ለመጎብኘት የሚመጡ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ቱሪስቶችን በቀጥታና በምቾት ለማስተናገድ በዕጅጉ እንደሚረዳም ነው የተናገሩት።
በተጨማሪም የንግድና የኢንቨስትመንት ፍሰቱን በመጨመር ምርቶችን በፍጥነት ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ፣ በአቪዬሽን፣ በሆቴልና በትራንስፖርት ዘርፎች ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር እንዲሁም ባሕር ዳርን የዓለም አቀፍ ስብሰባዎችና ሁነቶች ማዕከል ለማድረግ ከፍተኛ አቅምን እንደሚፈጥር አመልክተዋል።
ፕሮጀክቶችን አቅዶ መጀመር፣ በጥራት ፈጽሞ ለህዝብ አገልግሎት ማብቃት የመደመር መንግሥት ባህልና መገለጫ መሆኑን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ የትጋትና የመፈጸም ጉዟችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የውበት፣ የልምላሜና የፀዳል ተምሳሌት የሆነሽው ውቧ ባሕር ዳርና የአካባቢው ማህበረሰብ እንኳን ደስ አላችሁ! ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።