የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሀገራዊ ግብን በተደመረ አቅም የማሳካት ባህልን እያጎለበተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሀገራዊ ግብን በተደመረ አቅም የማሳካት ባህልን እያጎለበተ ነው
ሮቤ ፤ ሐምሌ 30/2018 (ኢዜአ) ፦ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሀገራዊ ግብን በተደመረ አቅም የማሳካት ባህልን ከማጎልበት ባሻገር ለቀጣዩ ትውልድ አሻራ ማኖርን ያስተማረ ነው ሲሉ የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።
ኢትዮጵያ በአንድ ጀምበር ከ805 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ለአፍሪካ ተምሳሌት መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መግለጻቸው ይታወሳል።
በዚህም ሀገሪቱ ከራሷ አልፋ ለመላው አፍሪካ ታላቅ ምሳሌ ለመሆን መቻሏን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብስረዋል።
የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን አንድምታ በተመለከተ ኢዜአ ከመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ምሁራን ጋር ቆይታ አድርጓል።
ምሁራኑ እንዳሉት፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሀገራዊ ግብን በተደመረ አቅም የማሳካት ባህልን ከማጎልበት ባሻገር ለቀጣዩ ትውልድ አሻራ ማኖርን ጭምር ያስተማረ ነው።
ከዩኒቨርሲቲው ምሁራን መካከል የውኃና አካባቢ ጥበቃ ረዳት ፕሮፌሰር አለማየሁ አባታ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሲቆሙ ተአምር መስራት እንደሚችሉ ትልቅ ማሳያ ነው።
በሀገሪቱ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በየጊዜው በሚተከሉ ችግኞች የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ እያገዘ መምጣቱንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል፣ የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግና የሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን አብራርተዋል።
የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ኢትዮጵያውያን በአንድነት ለተመሳሳይ ዓላማ ሲቆሙ ተአምር መስራት እንደሚችሉ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ነው ያስረዱት።
በሀገሪቱ ዜጎች በ"ይቻላል" መንፈስ እውን የሆነው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የዚሁ ህብረትና የተደመረ ሀገራዊ አቅም ማሳያ እንደሆነ አውስተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የአካባቢ ሳይንስ መምህርና የደን ዘርፍ ተመራማሪው አቶ ኡመር አብደላ በበኩላቸው፣ ሀገሪቱ እያሳካችው ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከአካባቢ ጥበቃ ባሻገር ዘለቄታዊና ሁለንተናዊ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመዋል።
ባለፉት ዓመታት በዘርፉ በተከናወኑ ተግባራት የአፈር ለምነትን በመጠበቅና የመሬት መራቆትን በመከላከል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በተሰሩ ሥራዎች አበረታች ውጤቶች መታየት መጀመራቸውን አክለዋል።
እንዲሁም ዓለም አቀፍ ስጋት የሆነውን የአየር ንብረት መዛባትና ድርቅን በመቋቋም የግብርና ምርታማነትን ማሳደጉን አመልክተዋል።
በተጨማሪም በደንና አካባቢ ጥበቃ ዘርፍ በተሰሩ ሥራዎች ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ከመቻሉም ባሻገር፣ ህዝቡ ለአንድ ሀገራዊ ግብ በጋራ ችግኝ በመትከልና በመንከባከብ የህብረትና የአብሮነት ባህሉን የሚያጠናክርበት ትልቅ መድረክ እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል።
ምሁራኑ እንዳመለከቱት፣ እነዚህ ስኬቶች ኢትዮጵያውያን በራሳቸው እቅድ፣ አቅምና በጸና ህብረት ከተንቀሳቀሱ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚችሉ በተግባር ያረጋገጡ ማሳያዎች ናቸው።