በከተማ አስተዳደሩ የጤና ተቋማት በቴክኖሎጂ የተደገፈ ምቹና ፈጣን አገልግሎት እየሰጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በከተማ አስተዳደሩ የጤና ተቋማት በቴክኖሎጂ የተደገፈ ምቹና ፈጣን አገልግሎት እየሰጡ ነው
ጎንደር ፤ ሐምሌ 30/2018 (ኢዜአ) ፦ በጎንደር ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የጤና ተቋማት በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር በመዘርጋት የህክምና አገልግሎቱን ምቹ፣ ጥራት ያለውና ፈጣን ማድረግ መቻሉን የከተማ አስተዳደሩ ጤና መምሪያ አስታወቀ።
በከተማ አስተዳደሩ የሚገኘው የቅዱስ ገብርኤል ጤና ጣቢያ የዲጂታል አገልግሎት አሰራር ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ዛሬ ተካሂዷል።
የጎንደር ከተማ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰኢድ የሻው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ በከተማዋ የሚገኙ የጤና ተቋማትን ዲጂታላይዝ በማድረግ ከወረቀት ነፃ የሆነ፣ ፈጣንና ፍትሐዊ አገልግሎት መስጠት ተችሏል።
በከተማዋ ከሚገኙ ስምንት ጤና ጣቢያዎች ውስጥ አምስቱ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር እውን በማድረግ ይነሱ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መቅረፍ መቻላቸውን ገልጸዋል።
በዚህም የመረጃ አያያዝን በማዘመን፣ የሕሙማንን እንግልት በመቀነስና የባለሙያዎችን ጊዜ በመቆጠብ ፈጣንና ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት መስጠት መቻሉን አስረድተዋል።
መምሪያውም በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 77 ሚሊዮን ብር ለጤና ተቋማቱ በመደገፍ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግንባታና የግቢ ማስዋብ ሥራው ውጤታማ እንዲሆን ማገዙን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የአጋር አካላትንና የማህበረሰቡን አቅም በማቀናጀት ሌሎች የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን ከማቀላጠፍ ባሻገር የሕክምና መሣሪያዎችና የመድኃኒት አቅርቦት የማሟላት ሥራ መሠራቱን አውስተዋል።
በጎንደር ከተማ አስተዳደር የቅዱስ ገብርኤል ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ታጀበ ታዬ እንደገለጹት፣ የወረቀት አልባ አሰራር የታካሚዎችን ምልልስና እንግልት ያስቀረ ነው።
ታካሚዎች በየቦታው ወረፋ በመጠበቅ የሚያባክኑትን ጊዜና የሚደርስባቸውን እንግልት በማስቀረት አስተማማኝ ሕክምና እንዲያገኙ ማስቻሉንም ተናግረዋል።
ይህም ደንበኞች በሕክምና አሰጣጡ ላይ ያነሱት የነበረውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍ ማስቻሉን አስረድተዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ደብሬ የኋላ እንደገለጹት፣ የከተማ አስተዳደሩ የሕክምና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍናና ጥራትን ለማሻሻል በቅንጅት እየሠራ ይገኛል።
በተጠናቀቀው ዓመት ብቻ አስተዳደሩ ለስምንቱም ጤና ጣቢያዎች ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል በጀት በመመደብ ዘመናዊ አሰራርን እንዲተገብሩ መደገፉን ገልጸዋል።
ይህም የጤና ተቋማቱን ግቢና አካባቢውን ጽዱ፣ ውብና ማራኪ በማድረግ በከተማዋ ከተገነባው የኮሪደር ልማት ጋር የተጣጣመ እንዲሆን የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
በቀጣይም የሕክምና ተቋማቱን አሰራር ሳይንሳዊና ዘመናዊ በማድረግ ለኅብረተሰቡ ጥራት ያለው፣ ቀልጣፋና አስተማማኝ ሕክምና እንዲሰጡ ለማስቻል እንደሚሠራ አመላክተዋል።