በባህር ዳር የተጀመሩ የኢኮኖሚና የመሰረተ ልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በባህር ዳር የተጀመሩ የኢኮኖሚና የመሰረተ ልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 30/2018 (ኢዜአ)፦ባህር ዳር የልማትና የእድገት ምሳሌ ሆና እንድትቀጥል የተጀመሩ የኢኮኖሚና የመሰረተ ልማት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በባህርዳር ከተማ የደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተርሚናል ዛሬ መርቀው ከፍተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምርቃቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ባህርዳር በተፈጥሮ ውበቷና በታሪካዊ እሴቶቿ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለጠቅላላው የአፍሪካ አህጉር የልማትና የእድገት ምሳሌ መሆን የምትችል ከተማ መሆኗን ገልጸዋል።
ከተማዋ ከመቶ ዓመታት በፊት በሸዋ፣በወለጋ እና በጎንደር መካከል ይደረግ ለነበረው ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ እንደ ዋና መሸጋገሪያ ድልድይ ሆና ስታገለግል መቆየቷን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህም ታሪካዊ አሰፋፈር ለክልሉ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ትልቅ መነሻ መሆኑን አስረድተዋል።
በጎርጎራ እና በባህርዳር መካከል የነበረውን ጥንታዊ የንግድና የቱሪዝም ትስስር ለማጠናከር በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣የጎርጎራ ሪዞርት እና የፈለገ ግዮን ፕሮጀክቶች መገንባታቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም እንደ ጣናነሽ ያሉ ትላልቅ መርከቦች በጣና ሀይቅ ላይ እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ በሁለቱ አካባቢዎች ያሉ ታሪካዊ ደሴቶችንና ቅርሶችን ለጎብኚዎች ምቹ የማድረግ ስራ ከመንግስት አልፎ በግሉ ዘርፍም በትኩረት እየተሰራበት ይገኛል ነው ያሉት።
ባህርዳር ከቱሪዝም በተጨማሪ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ከፍተኛ እቅም ያላት በመሆኗ የኢንዱስትሪ ፓርክ እንደተገነባላትም ነው የጠቀሱት።
ከተማዋ በሀገር ደረጃ በምሳሌነት የሚጠቀስ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ዲዛይንና ግንባታ ያላት መሆኑን ጠቁመዋል።
አክለውም በአካባቢው የተገነባው ታላቅ ድልድይ እና በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማት ከተማዋን የበለጠ ውብና ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ምቹ የሚያደርጋት መሆኑን አብራርተዋል።
በከተማዋ እየተገነባ ያለው ስታዲየም ሲጠናቀቅ ከሀገር ውስጥና ከአፍሪካ በርካታ ሰዎችን የሚስብ እንደሚሆንም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተከናወነውን የሪፎርም ስራ አድንቀዋል።
የፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ከቢሯቸው ሆነው በመላው ክልሉ የሚደረጉ ችሎቶችን በቨርቹዋል ለመከታተልና የህዝብን ቅሬታ ለመስማት የሚያስችል ዘመናዊ አሰራር በመዘርጋታቸው ምስጋና አቅርበውላቸዋል።
አዲሱን የአውሮፕላን ማረፊያ ተርሚናል ግንባታ በተመለከተም፣ ቀድሞ የነበረው አሮጌ ተርሚናል በግጭት ምክንያት ጉዳት ቢደርስበትም፤ በችግሩ ከመበሳጨት ይልቅ አጋጣሚውን ወደ እድል በመቀየር ለቀጣይ ትውልድ የሚሻገር የተሻለና የላቀ ተርሚናል መገንባት መቻሉን ተናግረዋል።
ይህ አሰራርና ችግርን ወደ መልካም አጋጣሚ የመቀየር ባህል ወደፊትም ሊደገምና ሊጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።
አዲሱ የደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተርሚናል ከአብዛኞቹ የአፍሪካ ዋና ከተሞች ኤርፖርቶች የተሻለ አቅምና ደረጃ ያለው መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህንን ታላቅ እቅም ወደ ሙሉ ስኬት ለመቀየር የህዝቡ ትጋት፣ ጥረትና የጋራ ስራ አስፈላጊ በመሆኑ፣ህዝቡ ጊዜውንና እድሉን ተጠቅሞ ለልማት እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
በተጨማሪም ሰላም ውድ ስጦታ፣ጊዜ ደግሞ ትልቅ ሀብት መሆኑን በማስገንዘብ፣ ህዝቡ በህብረት እንዲቆምና ሀገሩን እንዲያለማ ጠይቀዋል።
ልዩነቶች ወይም አለመግባባቶች ቢኖሩ እንኳ እንደ ጨዋ ህዝብ በንግግርና በውይይት መፍታት እንደሚገባ፤ ነገር ግን በግጭት ጊዜ ማባከን እንደማይገባ በአፅንኦት አሳስበዋል።
ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ውስጥ ክልሉና ባህርዳር ከተማ ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ የሚያስተዳድሩበት የተሟላ እድል አግኝተው እንደማያውቁ አውስተዋል።
አሁን ግን በህግ በተሰጣቸው ስልጣን መሰረት መስራትና ማሰራትን የሚችሉ የክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሉ ገልጸው፣ሁሉም ተባብሮ ባህርዳርን እንዲያለማ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።