የባህር ዳር አውሮፕላን ማረፊያ ዘመናዊ ተርሚናል ለሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ በረራዎች አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የባህር ዳር አውሮፕላን ማረፊያ ዘመናዊ ተርሚናል ለሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ በረራዎች አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 30/2018 (ኢዜአ) ፦ የባህር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲሱ ተርሚናል ለሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ በረራዎች አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የባህር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲሱን ተርሚናል ዛሬ መርቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ይህ ለኢትዮጵያ ቁልፍ የበረራ በሮች አንዱ ለሆነው አውሮፕላን ማረፊያ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን ጠቁመው፣ ፕሮጀክቱ ከዘመናዊ ተርሚናል በላይ ትርጉም እንዳለው አመልክተዋል።
ባህር ዳር በቅርብ ጊዜያት ካስተናገደቻቸው ፈተናዎች ማግስት የዚህ ተርሚናል ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መጀመር የፅናት፣ የማገገም እና ቀጣይነት ያለው ኢንቨስትመንት ማረጋገጫ መሆኑንም አብራርተዋል።
አዲሱ ተርሚናል ሰፊ የአውሮፕላን ማቆሚያዎችን፣ የላቁ መሰረተ ልማቶችን፣ የተስተካከሉ መዳረሻ መንገዶችን እና ዘመናዊ መገልገያዎችን ያካተተ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ይህም የአውሮፕላን ማረፊያውን የመቀበል አቅም በማሳደግ የአካባቢውን እያደገ የመጣ ፍላጎት የሚያሟላ ሲሆን፣ ለመንገደኞችም ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት እንደሚሰጥ አመልክተዋል።
ይህ አዲስ ተርሚናል ከተማዋን እያደሰ ካለው የከተማ ትራንስፎርሜሽን ጋር ተዳምሮ ባህር ዳርን ለዓለም አቀፍ እና ለሀገር ውስጥ በረራዎች ሌላኛዋ ቁልፍ መዳረሻና ማዕከል እንደሚያደርጋትም ጠቁመዋል።
ባህር ዳርን የመሰለች ንቁ ከተማ የምታስገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማረጋገጥ የአካባቢው ማህበረሰብ ሰላሙን መጠበቁን እንደሚቀጥል ተስፋ አደርጋለሁ ሲሉም ገልጸዋል፡፡