ቀጥታ፡

የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ የብዝሃሕይወት መመናመንን በመከላከል ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው

አሶሳ፤ ሐምሌ 30/2018 (ኢዜአ) ፦የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ የአካባቢ ብክለትን እና የብዝሃሕይወት መመናመንን በመከላከል ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የፌደራል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ። 

ንቅናቄው የህብረተሰቡን የአካባቢ ጥበቃ ግንዛቤ እያሳደገ መምጣቱም ተመላክቷል።

የፌደራል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አካባቢ፣ ደን ሃብት ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ጋር በመተባበር "ጽዱ ኢትዮጵያ ለትውልድ" በሚል መሪ ሃሳብ 3ኛውን ዙር የአካባቢ ብክለት መከላከል የ6 ወራት ንቅናቄ አስጀምሯል።


 

የፌደራል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ፍሬነሽ መኩሪያ እንደተናገሩት፤ የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ የአካባቢ ጥበቃ ሥራን ህዝባዊ  መሰረት በማስያዝ  አበረታች ውጤት አስገኝቷል።

የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ የአካባቢ ብክለትን፣ የብዝሃሕይወት መመናመን እና የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ  አይነተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ብለዋል።

ኢትዮጵያ 32ኛውን የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን (COP-32) በፈረንጆቹ ህዳር 2027 ለማዘጋጀት መመረጧ በአገር አቀፍ ደረጃ ለምታከናውናቸው ውጤታማ የአካባቢ ጥበቃ እና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች የተሰጠ ትልቅ ዓለም አቀፍ እውቅና መሆኑንም ጠቁመዋል።


 

ህብረተሰቡንና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከልና ብዝሀ ህይወትን ለመጠበቅ በትኩረት መሰራቱን ያነሱት ደግሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አካባቢ፣ ደን ሃብት ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሉቅማን አብዱልቃድር ናቸው።

የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ‎የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትን በማዘመን አካባቢን ውብ እና ጹዱ ከማድረግ ባለፈ ጤናማ ማኅበረሰብን ለመገንባት የተጀመረውን ጥረት ማጠናከር እንዳስቻለም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም