በምስራቅ ጎጃም ዞን በተለያዩ ዘርፎች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ጎጃም ዞን በተለያዩ ዘርፎች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተከናወነ ነው
ደብረ ማርቆስ፤ ሃምሌ 30/2018 (ኢዜአ)፡-በምስራቅ ጎጃም ዞን በተለያዩ ዘርፎች በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች መከናወናቸውን የዞኑ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ኃላፊ ወይዘሮ አሞኘሽ መሀመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ አብሮነትን የሚያጠናክሩና የዜጎችን የትብብር ባህል የሚያሳድጉ የክረምት በጎ ፈቃድ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በክረምቱ የዜጎች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እስካሁን ከ200 ሺህ በላይ የሚሆኑትን ተደራሽ ለማድረግ ተችሏል ብለዋል ።
እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለውም ከ460 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ እንደሆነ ተናግረዋል።
ከተከናወኑት ተግባራት መካከልም ከ47 ሺህ በላይ ችግኝ መትከል፣ ከ240 በላይ የአቅመ ደካሞች ቤቶችን በአዲስ መገንባትና መጠገን፣ እንዲሁም ከ21 ሺህ ሄክታር በላይ የአቅመ ደካሞች መሬትን በዘር የመሸፈን ስራ ይገኙበታል ነው ያሉት።
በተጨማሪም የመማሪያ ቁሳቁሶችን የማሰባሰብ ስራ፣ የደም ልገሳና ሌሎች ተግባራትን ማከናወን መቻሉን ጠቁመው፣ በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋጽኦ ማበርከት መቻሉን አብራርተዋል።
በዞኑ የአዋበል ወረዳ የወጀል ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ሙላት ጤናው በበኩሉ፣ በዚህ ክረምት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአቅመ ደካሞችን ቤት በመጠገንና ደም በመለገስ ስራ እየተሳተፈ እንደሚገኝ ተናግሯል።
ለወደፊትም ስራውን አጠናክሮ በማስቀጠል አቅመ ደካሞችን በጉልበቱ፣ በእውቀቱና በገንዘቡ ለመርዳት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
የአነደድ ወረዳ የአንበር ከተማ ነዋሪ ወጣት ሳሙኤል ሁነኛው በበኩሉ፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አራት ዓመት እንደሆነው ገልጿል።
በበጎ ፈቃድ ስራው በመሳተፉም አቅመ ደካሞችን ከመርዳት ባሻገር ከማህበረሰቡ ልምድና እውቀት በማግኘት ተጠቃሚ መሆኑን አስረድቷል።
በዞኑ ባለፈው ዓመት ክረምት በተካሄደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የልማት ተግባራትን ማከናወን መቻሉን ከመምሪያው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።