ቀጥታ፡

በምክክሩ የተተገበረው የተመካካሪዎች አደረጃጀት ሁሉም ለሀገር ይበጃል የሚለውን ሀሳብ እንዲሰጥ ዕድል ፈጥሯል

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 30/2018 (ኢዜአ) ፦ በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ተግባራዊ የተደረገው የተመካካሪዎች አደረጃጀት ሁሉም ለሀገር የሚበጀውን ሀሳብ እንዲገልጽ ከማስቻሉም በላይ አሳታፊነቱን ይበልጥ ለማረጋገጥ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ተመካካሪዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ አራት ሺህ ተመካካሪዎችን በማሳተፍ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ ይገኛል።

ተመካካሪዎቹ ኮሚሽኑ ይፋ ባደረጋቸው ስምንት አበይት የመመካከሪያ አጀንዳዎች ላይ እየተመካከሩ ሲሆን አሳታፊነትንና የሀሳብ ብዝሃነትን ማስተናገድ በሚያስችል መልኩ በተለያዩ ቡድኖች ተደራጅተዋል።

ይህም አስር፣ ሃምሳ፣ ሁለት መቶ ሃምሳ እና አምስት መቶ ሰዎችን በሚይዙ ቡድኖች ተደራጅተው እየተመካከሩ መሆኑ ይታወቃል።

ተመካካሪ መሰረት ማቲዎስ ለኢዜአ እንደገለጹት ተመካካሪዎች በተፈጠረላቸው አደረጃጀት ሀሳባቸውን በነጻነት እየገለጹና በተቀራረቡ ሀሳቦች ወደ መግባባት እየመጡ መሆኑን ተናግረዋል።

ምክክሩ ለሀገር አንድነትና ሰላም መጽናት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።


 

ሌላኛው ተመካካሪ አስቻለው አደራ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ተመካካሪዎች ትልቁን ሀገራዊ ማዕቀፍ በማሰብ ለሀገር የሚበጁ ሀሳቦች ላይ ወደ መግባባት እየደረሱ መምጣታቸውንና ምክክሩ በበጎ መልኩ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

ምክክሩ የሚደረግበት የቡድን አደረጃጀትም ተመካካሪዎች ሀሳባቸውን በነጻነት እንዲያነሱ እና አሳታፊነቱንም ለማጠናከር ጥሩ ዕድል ፈጥሯል ነው ያሉት።

ተመካካሪዎች ለሀገር ይበጃል የሚሉትን ሃሳብ በነጻነትና አሳታፊ በሆነ መልኩ ማቅረብ በሚችሉባቸው ቡድኖች መደራጀታቸው የሁሉንም ተመካካሪዎች ሀሳብ ማስተናገድ የሚያሰችል ዕድል መፍጠሩን የገለጹት ደግሞ ሌላኛው ተመካካሪ ሀይለእየሱስ ታዬ (ዶ/ር) ናቸው።


 

የምክክር ሂደቱ አስር፣ ሃምሳ፣ ሁለት መቶ ሃምሳ ከዛም አምስት መቶ ሰዎችን በያዙ ቡድኖች ተደራጅቶ መከናወኑ አሳታፊነትን መተግበር ተመካካሪዎች ሀሳባቸውን በነጻነት እንዲያነሱ እንዳስቻለም ገልጸዋል።

በመሆኑም ከምክክሩ የሚገኙ ምክረ ሃሳቦች ለበርካታ ዓመታት የልዩነት ምንጭ ሆነው የቆዩ ጉዳዮችን ለመፍታት ያስችላሉ ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል።

የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶችን በመወከል የምክክር ሂደቱን እየታዘቡ መሆኑን የተናገሩት ለሚ ስሜ ምክክሩ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል በማካተት ተመካካሪዎች ሃሳባቸውን በነጻነት እንዲያነሱ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ነው የገለጹት።


 

ተመካካሪዎች በንቃት እየተሳተፉ መሆንና በምክክሩም ደስተኛ መሆናቸውን መታዘባቸውን ገልጸው፤ ምክክሩ ሀገር መገንባት የሚያስችል የጋራ መፍትሔ ለማመላከት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም