ምክክሩ ለዘመናት ስር የሰደዱ ችግሮችን በመፍታት ለሀገራዊ መግባባት መሠረት የሚጥል ነው - ኢዜአ አማርኛ
ምክክሩ ለዘመናት ስር የሰደዱ ችግሮችን በመፍታት ለሀገራዊ መግባባት መሠረት የሚጥል ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 30/2018 (ኢዜአ) ፦ አካታችና አሳታፊ የሆነው ሀገራዊ ምክክር ለዘመናት ስር የሰደዱ ችግሮችን በመፍታት ለሀገራዊ መግባባት መሠረት የሚጥል ነው ሲሉ ተመካካሪዎች ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በማሳተፍና ስምንት የምክክር አጀንዳዎችን በመለየት ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ የምክክር ጉባዔ እየተካሄደ ይገኛል።
በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ በሚገኘው ምክክር አራት ሺህ ተመካካሪዎች እየመከሩ ይገኛሉ።
ተሳታፊዎቹ ምክክሩ ልዩነቶችን በምክክር በመፍታት፣ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠርና ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት ወሳኝ ሚና እንዳለውም ጠቅሰዋል፡፡
ተመካካሪ አቶ መሳሪያው ተንጎ ምክክሩ ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች በማሳተፍ አካታችነቱ የተረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡
በሂደቱ ሁሉም ተመካካሪዎች ሃሳባቸውን በነፃነት እያቀረቡ መሆናቸውን ጠቅሰው ለሀገር ዕድገት የሚበጁና ጠንካራ ሀገረ መንግስት መገንባት የሚያስችሉ ሃሳቦች እየተንሸራሸሩ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
ከምክክሩ በኋላ ሀገራዊ መግባባቷ የተጠበቀና አንድነቷ የተረጋገጠባት ጠንካራ ሀገር እንደሚገነባም ጠቁመዋል፡፡
ተመካካሪ ወይኒቱ አዱኛ የሀገራዊ ምክክሩ ሂደት አሳታፊነቱን በጠበቀ መልኩ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
ሂደቱ አካታችና ነፃ የሀሳብ ልውውጥ የሚደረግበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ሴቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ያካተተ መሆኑን አንስተዋል።
አክለውም ከዚህ ምክክር በኋላ አንድነቷ የተጠናከረና ሰላሟ የበዛ ኢትዮጵያ እንደምትገነባም ተስፋቸውን ተናግረዋል።
ተመካካሪ ሻም አሜ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ በመሆኗ ሂደቱም በፍቅር፣ በሰላምና በመግባባት የሕዝቦችን አንድነት ለማጠናከር እጅግ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።