ቀጥታ፡

አረንጓዴ ዐሻራ መርሀ-ግብር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ የልማት ግቦች በማሳካት በኩል ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ነው

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 30/2018 (ኢዜአ) ፦ አረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር የኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚ የልማት ግቦች በማሳካት በኩል ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ገለጸ።

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አመራር አባላት እና ሰራተኞች በቢሾፍቱ ፍጥነት መንገድ ዳርቻ አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል።


 

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት የተጀመረው አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን እያስገኘ ነው።

መርሃ-ግብሩ የአመራር እና የህዝብ ቁርጠኝነት የታየበት ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ የታየበት ተጨባጭ ለውጦችን ያመጣ መሆኑንም ተናግረዋል።

አረንጓዴ ዐሻራ የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙ ከማስቻል ባለፈ የደን ሽፋን እንዲጨምር በማድረግ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣውን ተጽዕኖ መከላከል ማስቻሉንም ጠቅሰዋል።

የካርቦን ሽያጭን በማጠናከር ኢትዮጵያ ከካርቦን ሽያጭ የምታገኘው ገቢ እንዲያድግም መርሃ-ግብሩ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በመርሃ-ግብሩ ለምግብነት የሚውሉ በርካታ የፍራፍሬ ችግኞች እየተተከሉ መሆኑን አስታውሰው፤ ይህም የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከመሸፈን ባለፈ የውጭ ምንዛሬ እንዲገኝ እያስቻለ ነው ብለዋል።


 

አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር የኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚ የልማት ግቦችን በማሳካት በኩል ተጨባጭ ውጤቶችን እያስገኘ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሚኒስቴሩ የመሰረታዊ አገልግሎት ስራ አስፈፃሚ መልካሙ ተሰማ በበኩላቸው፤ ዛሬ የምንተክለው ችግኝ ለቀጣዩ ትውልድ ቅርስ ነው፤ በመርሀ ግብሩ በመሳተፌ ደስተኛ ነኝ ብለዋል።

በችግኝ ተከላ ላይ በተለያዩ ጊዚያት መሳተፋቸውን የገለጹት ወይዘሮ ጸሀይ በቀለ በበኩላቸው፤ ዛሬ የምንተክለው ለትውልዱ አርአያ ለመሆንም ጭምር ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በቀጣይም ችግኝ በመትከልና በመንከባከብ በኩል የሚጠበቅብኝን ሃላፊነት በሚገባ ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም