ምክር ቤቱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባካሄደው ክትትልና ድጋፍ ውጤታማ አፈፃፀም እንዲመዘገብ አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባካሄደው ክትትልና ድጋፍ ውጤታማ አፈፃፀም እንዲመዘገብ አድርጓል
ወልቂጤ፤ ሐምሌ 30/2018(ኢዜአ)፦ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባካሄደው ክትትልና ድጋፍ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ዕቅዶች ተግባራዊ ሆነው ውጤታማ አፈፃፀም እንዲመዘገብ ማድረጉን ገለጸ።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 6ኛ መደበኛ ጉባኤውን በወልቂጤ ከተማ እያካሄደ ነው።
የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ፋጤ ሰርሞሎ በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት፤ ምክር ቤቱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባካሄደው ክትትልና ድጋፍ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ዕቅዶች ተግባራዊ ሆነው ውጤታማ አፈፃፀም እንዲመዘገብ አድርጓል።
ለዚህም የምክር ቤቱ አባላትም በቋሚ ኮሚቴዎች አማካይነት በአካል ክትትል ማድረጉንና ዕቅድና ሪፖርቶችን በማመሳከር የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣታቸውን ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ የክልሉን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ የልማት ሥራዎች እንዲሳኩ ክትትል በማድረግ ግብረ መልስ ከመስጠት ባለፈ፣ ተጠያቂነትን በማስፈን የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣቱን አስረድተዋል።
ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ጉባኤም በ2018 በጀት ዓመት የአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ዕቅድ አፈጻጸም እና በ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።
ምክር ቤቱ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ በዋና ኦዲተር እና በምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት አፈጻጸም እንዲሁም በያዝነው በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅዶች ላይ በዝርዝር ተወያይቶ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍም ይጠበቃል።
በተጨማሪም የክልሉ የ2019 በጀት ዓመት የሥራ ማስፈጸሚያ በጀት ለምክር ቤቱ ቀርቦ እንደሚጸድቅም ከወጣው መርሃ ግብር ለመረዳት ተችሏል።