ምክክሩ ለዘላቂ ሰላምና የተሻለች ኢትዮጵያን ለትውልዱ ለማስረከብ ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ምክክሩ ለዘላቂ ሰላምና የተሻለች ኢትዮጵያን ለትውልዱ ለማስረከብ ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት ነው
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 30/2018 (ኢዜአ) ፦ ምክክሩ ለዘላቂ ሰላምና የተሻለች ኢትዮጵያን ለትውልዱ ለማስረከብ ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት ነው ሲሉ ተመካካሪዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱ ቀጥሏል።
በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በስምንት ዐበይት ሀገራዊ አጀንዳዎች ዙሪያ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ጥልቅና አሳታፊ ምክክር እያካሄዱ ይገኛል።
ተመካካሪ አቶ ምስጋናው ስማቸው ለኢዜአ እንዳሉት በምክክር ጉባኤው ተሳታፊዎች ሀሳባቸውን በነጻነት የሚያነሱበት መሆኑን ገልጸው፤ ምክክሩ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር በሚያስችል ሂደት ላይ ነው ብለዋል።
ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሁም የተሻለች ኢትዮጵያን ለትውልዱ ለማስረከብ ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት መሆኑንም ተናግረዋል።
ሌላኛዋ ተመካካሪ ወይዘሮ ጸጋነሽ በቀለ በበኩላቸው በምክክር ሂደቱ ሀሳቦች በነጻነት የሚስተናገዱና መግባባት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸዋል።
የምክክር ጉባኤው ዘላቂ ሰላሟ የተረጋገጠ፣ ለልማትና ለዜጎቿ ምቹ የሆነች ሀገርን ለመገንባት ወሳኝ መድረክ ነው ብለዋል።
የምክክር መድረኩ ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍል የተወጣጡ ተመካካሪዎች በአንድ ሆነው ሃሳባቸውን የሚገልጽበት ትልቅ ሃገራዊ ጉባኤ ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛው ተመካካሪ አቶ ሃብታሙ አስፋው ናቸው።
ተመካከሪዎች ሀሳባቸውን ያለምንም ስጋት በነጻነት እያነሱ መሆኑን ገልጸዋል።