ቀጥታ፡

የሲቪል ምዝገባ የዲጂታል ስርዓት ዜጎች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ እያስቻለ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 30/2018 (ኢዜአ) ፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ የጀመረው ዲጂታል የአሰራር ስርዓት ዜጎች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ እያስቻለ መሆኑን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዮሴፍ ንጉሤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ አሰራሩን ለማዘመንና ለማቀላጠፍ አገልግሎቶቹን በኦንላይን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

የኦንላይን አገልግሎቱ ገፅ ለ ገፅ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች በተሻለ ሁኔታ ዜጎች ካሉበት ቦታ ሆነው በሞባይል፣ በላፕቶፕና በሌሎች ዲጂታል መሳሪያዎች በአጭር ጊዜ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።


 

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዮሴፍ ንጉሤ ለኢዜአ እንደገለጹት ፤ ተቋሙ በአጠቃላይ ከሚሰጣቸው ሰባት ዋና ዋና አገልግሎቶች መካከል በአሁኑ ወቅት የመታወቂያ፣ የልደት እና ያላገባ ማረጋገጫ አገልግሎቶችን በኦንላይን እየሰጠ ይገኛል።

እስከ አሁን ከ15 ሺህ በላይ ተገልጋዮች በኦንላይን ሥርዓቱ አገልግሎት ማግኘታቸውን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፤ አዲሱ አሰራር የተገልጋዮችን ጊዜና ወጪ ከመቆጠቡም በላይ እንግልትን እያስቀረ መሆኑን አስረድተዋል።

በተጨማሪም አሰራሩ ለባለሙያዎች ምቹ የሥራ ሁኔታ በመፍጠር የሥራ ቅልጥፍናንና ውጤታማነትን ማሳደጉን ገልጸዋል።

ኤጀንሲው መረጃዎችን በዲጂታል ሥርዓት በማደራጀት ዘመናዊ የኦንላይን አገልግሎቶችን በስፋት ተደራሽ የማድረግ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።

በቀጣይም የጋብቻ፣ የፍቺ፣ የሞትና የጉዲፈቻ አገልግሎቶችን ጨምሮ ሌሎችንም አገልግሎቶች ወደ ኦንላይን ሥርዓት በማስገባት ተደራሽነታቸውን ለማሳደግ እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ከጤና ተቋማትና ከፍርድ ቤቶች ጋር በመቀናጀት እንደ ልደትና ሞት ያሉ ኩነቶች በተከሰቱበት ቦታ ላይ በቀጥታ እንዲመዘገቡ የሚያስችል አሰራር እየተጠናከረ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

በኤጀንሲው እየተከናወነ ያለው ይህ የዲጂታል ሽግግር የኢትዮጵያን የዲጂታል 2030 ስትራቴጂ እና የከተማዋን የስማርት ከተማ ግንባታ ግብ እውን ለማድረግ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረውም አብራርተዋል፡፡

አገልግሎቱን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ በመገናኛ ብዙኃንና በተለያዩ አማራጮች ህብረተሰቡ ስለ ኦንላይን አገልግሎቱ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ እየተሰራ መሆኑ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም