ሀገራዊ ምክክሩ የቆዩ ችግሮችን በምክክር በመፍታት ለዘላቂ ሰላምና እድገት መሰረት ይጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ የቆዩ ችግሮችን በምክክር በመፍታት ለዘላቂ ሰላምና እድገት መሰረት ይጥላል
ሚዛን አማን፣ ሐምሌ 30/2018 (ኢዜአ)፡-ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት የቆዩ ችግሮችና ልዩነቶችን በምክክር በመፍታት ሰላምና እድገትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ጠንካራ መሰረት እንደሚጥል የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በማሳተፍ እየተካሄደ ያለውና የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ የደረሰው ሀገራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ ታሪካዊ አጋጣሚ እንደሆነም ተናግረዋል።
ኢዜአ በሚዛን አማን ከተማ ካነጋገራቸው ነዋሪዎች መካከል አቶ እጅጉ ጉርሜሳ እንዳሉት አለመግባባቶችን በውይይት የመፍታት የማህበረሰቡን እሴቶች ወደ አደባባይ በማውጣት ለቆዩ ሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ሀገራዊ ምክክሩ የሄደበት ርቀት ተሰፋ ሰጪ ነው።
በኮሚሽኑ ለውይይት የተለዩ አጀንዳዎች የህዝብ አጀንዳ እንደሆኑና ለዘላቂ ሰላምና የህዝቦች አንድነት መፍትሄ ያመጣሉ ብለው እንደሚያምኑ የገለጹት አቶ እጅጉ፣ በተለይ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮች በምክክሩ እልባት ያገኛሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
በመተማመን ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት የሁሉንም ተሳትፎ እንደሚጠይቅና ሀገራዊ ምክክሩ በዚህ ሂደት ያለፈ መሆኑን ያመለከቱት ደግሞ ወይዘሮ ማርታ ሽቢ የተባሉ ነዋሪ ናቸው።
ህዝብን ወክለው በሀገራዊ ምክክሩ እየተሳተፉ ያሉ አካላት በተለዩ አጀንዳዎች ላይ በሀላፊት ስሜት በመወያየት ለሁሉም የምትመች ሀገርን በመገንባት ረገድ ያላቸውን ሚና በአግባቡ እንደሚወጡ እምነታቸውን ገልጸዋል።
በኮሚሽኑ ለውይይት የተለዩ አጀንዳዎች የኢትዮጵያ ህዝብ አጀንዳ ስለመሆናቸውና በምክክሩ ትልቅ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸው፣ በምክክሩ የሚሳተፉ ተወካዮቻቸው በሰለጠነ መንገድ በመወያየት ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ልማት የተጣለባቸውን ሀላፊነት በብቃት እንደሚወጡ ተስፋቸውን ገልጸዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን የሁሉም ንቁ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ደግሞ አቶ መንግሥቱ ሻምበል እና አቶ ግርማ አይነታ ናቸው።
ችግሮችን በመሰረታዊነት በምክክር ለመፍታት ኮሚሽኑ በገለልተኛነትና ሁሉን አሳታፊ በሆነ መንገድ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ልምድ የሚወሰድባቸው ናቸው ብለዋል።
ለምክክሩ በአጀንዳነት የለያቸው ጉዳዮችም በየደረጃው ህዝብ የተወያየባቸውን ሀሳቦች በአግባቡ አጠቃሎ የያዘ በመሆኑ የምክክሩን ስኬት እንደሚያጎላው ጠቁመዋል።
ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ ባለው የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ 4ሺህ የሕዝብ ወኪሎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።
ተመካካሪዎቹ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን የሚወክሉ ሲሆን ለውይይት በተለዩ ስምንት ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይም ጥልቅና አሳታፊ ምክክር እያካሄዱ ይገኛሉ።