ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና የብርና የነሐስ ሜዳሊያ አግኝታለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና የብርና የነሐስ ሜዳሊያ አግኝታለች
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 30/2018 (ኢዜአ) ፦ 21ኛው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 አመት በታች ሻምፒዮና ትናንት ማምሻውን በአሜሪካ ኦሬጎን ተጀምሯል።
ዛሬ ማለዳ ላይ በተካሄደው የሴቶች 5000 ሜትር ፍጻሜ አትሌት ሽቶ ጉሚ 15 ደቂቃ ከ07 ሴኮንድ ከ21 ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ አግኝታለች።
በዚሁ ውድድር ላይ የተሳተፈችው አትሌት እመቤት ጥላሁን 15 ደቂቃ ከ32 ሴኮንድ ከ51 ማይክሮ ሴኮንድ ስድስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
ዩጋንዳዊቷ አትሌት ቻሪቲ ቼሮፕ 15 ደቂቃ ከ03 ሴኮንድ ከ88 ማይክሮ ሴኮንድ አንደኛ ወጥታለች። ኬንያዊቷ ጆይሊን ቼፕኬሞይ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች።
በወንዶች 5000 ሜትር ፍጻሜ አትሌት ዳምጠው ከበደ 13 ደቂቃ ከ35 ሴኮንድ ከ38 ማይክሮ ሴኮንድ ሶስተኛ በመውጣት ለኢትዮጵያ የነሐስ ሜዳሊያ አስገኝቷል። በርቀቱም የግል ምርጥ ሰዓቱን አስመዝግቧል።
ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ማማሩ ጎዴ 13 ደቂቃ ከ44 ሴኮንድ ከ41 ማይክሮ ሴኮንድ አምስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
ኬንያዊው አትሌት ፍራንክሊን ኪቤት 13 ደቂቃ ከ28 ሴኮንድ ከ27 ማይክሮ ሴኮንድ አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል።
ሌላኛው ኬንያዊ ኔሄሚያ ኪፕጌንዮ ሁለተኛ ወጥቷል።
ከፍጻሜው በተጨማሪም በሻምፒዮናው መክፈቻ የማጣሪያ ውድድሮች ተደርገዋል።
በሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል የመጀመሪያ ማጣሪያ አትሌት አልማዝ ዮሀንስ 9 ደቂቃ ከ42 ሴኮንድ ከ45 ማይክሮ ሴኮንድ አንደኛ በመውጣት ወደ ፍጻሜ አልፋለች።
አትሌት ወሰኔ አሰፋ 9 ደቂቃ ከ56 ሴኮንድ ከ36 ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ወደ ፍጻሜው ውድድር ተሸጋግራለች።
የፍጻሜው ውድድር ነገ ይካሄዳል።
በወንዶች 800 ሜትር የመጀመሪያ ማጣሪያ የተሳተፈው አትሌት ነጋሄ እያሱ 1 ደቂቃ ከ51 ሴኮንድ ከ16 ማይክሮ ሴኮንድ አንደኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ ወደ ግማሽ ፍጻሜ አልፏል።
በሌላኛው የወንዶች 800 ሜትር የማጣሪያ ምድብ የተሳተፈው የሮሰን ግርማ 1 ደቂቃ ከ47 ሴኮንድ ከ57 ማይክሮ ሴኮንድ አራተኛ ደረጃን በመያዝ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል።
በሴቶች 800 ሜትር የመጀመሪያ ማጣሪያ የተሳተፈችው ደራርቱ ሽብሩ 2 ደቂቃ ከ10 ሰከንድ ከ28 ማይክሮ ሴኮንድ አምስተኛ በመውጣት ወደ ፍጻሜው አልፋለች።
እንዲሁም በሴቶች 800 ሜትር ምድብ አራት የተወዳደረችው ሀብታም ገበየሁ 2 ደቂቃ ከ04 ሴኮንድ ከ66 ማይክሮ ሴኮንድ አንደኛ ደረጃን በመያዝ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ተሸጋግራለች።
የ800 ሜትር የግማሽ ፍጻሜ ማጣሪያ ውድድሮች ነገ ይካሄዳሉ።