ቀጥታ፡

የመደመር ፍሬ፡አረንጓዴዋ ኢትዮጵያ

በሙሴ መለሰ

የመደመር እሳቤ ዋና መሠረቱ እውቀትን፣ጉልበትን፣ሀብትንና አቅምን አስተባብሮ ለአንድ የጋራ ዓላማ በጋራ ማቆምን ያመለክታል። ይህን የሃሳብ ልዕልና በተግባር ፈትሾ ተጨባጭ ውጤት የታየበት ላለፉት ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያ የተካሄደው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ነው።

አረንጓዴ ዐሻራ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በ2011 ዓ.ም ጅማሮውን አግኝቷል። የአረንጓዴ ዐሻራ ትልቁ ማሳያ የህዝብ ህብረት የታየበት መሆኑ ነው።

በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እድሜ፣ ጾታ እና ልዩነት ሳይበግራቸው በነቂስ በመውጣት በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል አኩሪ ታሪክ የሰሩበት ህዝባዊ ንቅናቄ የመደመርን አስተሳሰብ በተግባር ያረጋገጠ ነው።

ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሀሳብ ከተካሄደው የአንድ ጀምበር መርሃ ግብር እንደታየው፣መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ያለ ምንም ክፍያ በሙሉ ፈቃደኝነት እና በዝናብ ውስጥ ውሎ ከ805 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል አዲስ ታሪክ ሰርቷል። በአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላው 26 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች ተሳትፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ይህ ህዝባዊ ንቅናቄ ኢትዮጵያውያን ተደምረው ለነገ ልጆቻቸው መሰረት ለመጣል ሲወስኑ ምን ማድረግ እንደሚችሉ ለዓለም ህዝብ ያሳዩበት ህያው አብነት ነው።

የመደመር እሳቤ በቃላት ሳይሆን በተጨባጭ ውጤት የሚለካ ነው፤ በዘንድሮው የችግኝ ተከላ ዘመቻ እስካሁን 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፣ቀሪው 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ደግሞ በቀጣይ ጊዜያት ይተከላል።

በአንድ ወቅት ከ40 በመቶ በላይ የደን ሽፋን የነበራት ኢትዮጵያ ዘላቂ ያልሆነ የተፈጥሮ ሃብትና የመሬት አጠቃቀም ምክንያት የደን ሽፋኗ ወደ 3 በመቶ ወርዶ ነበር።

አረንጓዴ አሻራ ሀገራዊ የደን ሽፋን ከነበረበት 17.2 ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ በማሳደግ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። ችግኝ ተከላው ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ ከምግብ ዋስትና እና ከሀገር ኢኮኖሚ ጋርም የተሳሰረ ነው።

በፍራፍሬ እንደ አቮካዶ፣ማንጎ እና ቡና ባሉ ምርታማ ችግኞች ላይ በማተኮሩ የአፈር መሸርሸርን ከመከላከል ባሻገር፣ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የምትበለጽግ፣የማትለምን እና ለተቸገሩት የምትደርስ ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችል የዜጎችን ገቢ የማሳደግ ድርሻ አለው።

ኢትዮጵያ ችግኞችን ለጎረቤት ሀገራት በመስጠት ያከናወነቻቸው የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ስራዎች የመደመር እሳቤ ድንበር አቋርጦ ለአህጉራዊ ትስስር እና ለዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄ የሚሆን ድንበር ተሻጋሪ እሴት እንዳለው ያሳያል።

ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት እና የአካባቢ ጥበቃ ስራዋ 32ኛውን የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 32) እንድታስተናግድ ምክንያት ሆኗል።

ይህም የኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረት ዓለም አቀፍ እውቅናን አስገኝቷል።

በአጠቃላይ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ኢትዮጵያውያን በቀና እሳቤ እና በትብብር በመቆም ተስፋን ለልጆቻቸው መዝራት እንደሚችሉ በተግባር፣በስራና በውጤት ያረጋገጡበት ትልቅ ሀገራዊ ኩራት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም