በሆስፒታሉ የኦክስጅን ማምረቻ ማዕከልን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎት መስጫዎች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ተደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
በሆስፒታሉ የኦክስጅን ማምረቻ ማዕከልን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎት መስጫዎች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ተደረጉ
ባህርዳር ፤ ሐምሌ 29/2018 (ኢዜአ) ፦ በባህር ዳር ከተማ ፈለገ ህይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተገነባ የኦክስጅን ማምረቻ ማዕከልን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎት መስጫዎች የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በተገኙበት ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ተደረጉ።
በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዱልከሪም መንግስቱን ጨምሮ ሌሎች የዘርፉ የስራ ሀላፊዎች የተገኙ ሲሆን የሆስፒታሉ የስራ እንቅስቃሴም ተጎብኝቷል ።
በሆስፒታሉ ከኦክስጅን ማምረቻ ማዕከል በተጨማሪ የጨቅላ ህፃናት ህክምና ማዕከልና የዲጂታል ቋት ምረቃ የተካሄደ ሲሆን የተለያዩ አገልግሎቶችና የቀዶ ህክምና ክፍል የእድሳት ማስጀመሪያ ስነ ስርአት ተከናውኗል።
በሆስፒታሉ የኦክስጅን ማምረቻ ማዕከል መገንባት የህክምና አገልግሎት አሰጣጡን የተሟላ እንደሚያደርገው የሆስፒታሉ የባዮ ሜዲካል ክፍል አስተባባሪ ውዴ በቀለ ለኢዜአ ገልፀዋል።
ማእከሉ በአመት 28ሺህ 800 ሲሊንደር ኦክሲጅን የማምረት አቅም እንዳለው ጠቁመው ይህም ምርቱን ከሆስፒታሉ ባለፈ ለሌሎች በአካባቢው ለሚገኙ ጤና ተቋማት የማቅረብ አቅም እንደሚኖረው አመላክተዋል ። በስነ ስርአቱ የችግኝ ተከላ ተካሂዷል።
በነገው እለትም ሚኒስትሯ በተገኙበት በጤናው ዘርፍ የሚመክር መድረክ በባህር ዳር ከተማ እንደሚካሄድ ተመላክቷል።