ሀገራዊ ምክክሩ ሀገራዊ መግባባትን በመፍጠር የተሻለች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ማስረከብ የሚያስችል ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ ሀገራዊ መግባባትን በመፍጠር የተሻለች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ማስረከብ የሚያስችል ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2018 (ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ ሀገራዊ መግባባትን በመፍጠር የተሻለች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ የሚያስችል ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ተመካካሪዎች ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በማሳተፍ ስምንት የምክክር አጀንዳዎችን በመለየት ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ የምክክር ጉባዔ እየተካሄደ ይገኛል።
በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ በሚገኘው ምክክር አራት ሺህ ተመካካሪዎች እየመከሩ ይገኛሉ።
በምክክር ሂደቱ ላይ እየተሳተፉ ያሉ ተመካካሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሀገራዊ ምክክሩ ሀገራዊ መግባባትን በመፍጠር የተሻለች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ያስችላል።
የምክክር ሂደቱ ሁሉም ዜጋ ለሀገሩ የድርሻውን የሚያበረክትበት ትልቅ ዕድል የፈጠረ መሆኑን በመግለጽ፣ ለሀገር ግንባታ የሚረዱ ሀሳቦችን እያንሸራሸሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ተመካካሪ ከተማ ባህሩ እንደገለጹት፣ ሀገራዊ የምክክር ጉባዔው በአጀንዳዎች ዙሪያ ላይ የጋራ መግባባትን ለመፍጠር የሚያስችል ጠንካራ መድረክ ሆኖ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡
መድረኩ የሀሳብ ብዝሃነትን በአግባቡ የሚያስተናግድና ሁሉም ተመካካሪዎች ሃሳባቸውን በነጻነት እንዲያንሸራሽሩ ሰፊ ዕድል ያመቻቸ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በመሆኑም ሂደቱ ሁሉንም የህብረተሰቡን ክፍሎች ያሳተፈና አካታች በመሆኑ ለሀገራዊ አንድነትና ውይይት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ተመካካሪ እቴነሽ ሙሉጌታ በበኩላቸው፤ የምክክር ሂደቱ አካታች መሆኑን በመግለጽ፣ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችል ትልቅ ዕድል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ምክክሩ አንድነትን የሚያጠናክር መሆኑን በመጠቆም፣ ሁሉንም ያሳተፈ መሆኑንና በሁሉም ጉዳዮች ላይ በግልጽ እየተወያዩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
እያካሄድነው ያለው ሀገራዊ ምክክር ለመጭው ትውልድ ደህንነቷ የተጠበቀ እና ሰላሟ የተረጋገጠች ሀገር ለማስረከብ የሚያስችል ነው ያለው ተመካካሪ ደግሞ አብዱላዚዝ አብዲ ነው፡፡
ምክክሩ ሀገራዊ መግባባት የተፈጠረባት ኢትዮጵያን ለመገንባት ትልቅ ተስፋ እንዳለውም ተናግሯል።