ኢትዮጵያ 76ኛውን የዓለም ጤና ድርጅት ስብሰባ ታስተናግዳለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ 76ኛውን የዓለም ጤና ድርጅት ስብሰባ ታስተናግዳለች
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2018 (ኢዜአ)፦ 76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ኮሚቴ ስብሰባ (RC76) ከነሐሴ 18 እስከ 22 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
ስብሰባው ከዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር የሚዘጋጅ ነው።
በዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና መረጃ መሠረት፣ ስብስባው የቀጣናውን የጤና አጀንዳዎች ላይ መምከርና አህጉራዊ ትብብርን ማጠናከርን ያለመ ነው።
የ47ቱ የአፍሪካ ቀጣና አባል አገራት የጤና ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የዓለም አቀፍ ጤና መሪዎች፣ የልማት አጋሮች፣ ለጋሾችና የዓለም ጤና ድርጅት ተወካዮችን ጨምሮ ከ600 በላይ ተወካዮች በስብስባው ላይ ይሳተፋሉ።
የስብሰባው ተሳታፊዎች በቀጣናዊ የጤና አቅዶች ላይ የተመዘገቡ ውጤቶችን የሚገመግሙ ሲሆን በአዳዲስ ስትራቴጂዎችና የውሳኔ ሀሳቦች ላይ ይመክራሉ።
እንዲሁም የጤና ሥርዓቶችን ለማጠናከር፣ ሁለንተናዊ የጤና ሽፋን ተደራሽነትን ለማስፋፋት፣ የጤና ደህንነትን ለማሻሻልና የአደጋ ጊዜ ዝግጁነትን ለማሳደግ የሚረዱ የጋራ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ ህብረትና በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ካሶሎ፤ ስብሰባው አባል አገራት የቀጣናውን የጤና አጀንዳ እንዲቀርጹ፣ አጋርነታቸውን እንዲያጠናክሩ እና በመላው አፍሪካ ጤናማ፣ አስተማማኝና ጠንካራ ማህበረሰቦችን የመገንባት ሂደት ለማፋጠን ትልቅ እድል የሚሰጥ ነው ብለዋል።
ተወካዩ አክለውም የኢትዮጵያ ስብሰባውን ማስተናገድ፤ ለቀጣናዊ ወንድማማችነትና ለጋራ ትብብር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ አህጉራዊ ጉባኤ የኢትዮጵያን የጤና ሥርዓት ስኬቶች፣ በተለይም መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶችን በማስፋፋትና በቅርቡ በክልል የተከሰተውን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ተከስቶ የነበረውን የማርበርግ ቫይረስ በመቆጣጠር ረገድ የተመዘገቡ ውጤቶችን ለማሳየት ዕድል እንደሚፈጥር መረጃው አመልክቷል።
ስብስባው የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ፣ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን በመጠቀም ለጋራ የጤና ፈተናዎች የተቀናጀ አህጉራዊ ምላሽ ለመስጠት ስትራቴጂካዊ መድረክ እንድትሆን ያደርጋታል።
በስብስባው ላይ የቴክኒክ ውይይቶች፣ አውደ ርዕዮች ፣ የሁለትዮሽ ስብሰባዎችና የሕዝብ ግንኙነት ስራዎች የሚካሄዱ ሲሆን፣ እነዚህም በአፍሪካ ተቋማት መካከል የጤናው ዘርፍ የፈጠራ ስራዎችንና የእውቀት ልውውጥን የሚያጎሉ እንደሚሆኑ ተገልጿል።
የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ኮሚቴ የቀጣናዊ ጽሕፈት ቤቱ የበላይ አካል ሲሆን፤ በየዓመቱ በመሰብሰብ የቀጣናውን የጤና ፖሊሲ ይወስናል፣ የድርጅቱን ሥራዎች ይገመግማል፣ እንዲሁም በመላው አህጉሪቱ ለሚከናወኑ የጤና ተግባራት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን አጀንዳዎች ያስቀምጣል።