ቀጥታ፡

የደረጃ ‹‹ለ›› ግብር ከፋዮች እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በኦንላይን ክፍያ መፈጸም ይጠበቅባቸዋል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2018 (ኢዜአ) ፦የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ መልዕክት የደረሳቸው የደረጃ ‹‹ለ›› ግብር ከፋዮች እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በኦንላይን ክፍያቸውን በመፈጸም የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቀረበ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሰውነት አየለ በሰጡት መግለጫ፣ቢሮው የግብር ስርዓቱን በማዘመን እና ፍትሃዊ አሰባሰብን በመዘርጋት ገቢን በጥራት እየሰበሰበ ይገኛል ብለዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ከሚሰበስበው ገቢ 72 በመቶውን ለዘላቂ ልማት፣ ለሰው ተኮር ፕሮጀክቶች እና ለኮሪደር ልማት በማዋል የመዲናዋን ገጽታና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እያጎለበተ ይገኛልም ብለዋል።

በከተማዋ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች የተሰማሩ ከ456 ሺህ በላይ የደረጃ «ለ» ግብር ከፋዮች አዲስ በተሻሻለው የገቢ ግብር አዋጅ መሰረት ግዴታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

ከደረጃ ‹‹ለ›› ግብር ከፋዮች በዘንድሮ በጀት ዓመት 9.2 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸዋል።

መረጃቸው ለተሟላላቸው ግብር ከፋዮች የግብር ውሳኔ በስልክ የጽሁፍ መልዕክት የተላከ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ ግብራቸውን በወቅቱ መክፈላቸውን አንስተዋል።

እስከ ሐምሌ 25 ቀን 2018 ዓ.ም መልዕክት የደረሳቸው ግብር ከፋዮች እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በኦንላይን በመክፈል ከቅጣት እና ወለድ ራሳቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች መልዕክት ያልደረሳቸው ወይም ከሐምሌ 25 በኋላ የደረሳቸው ግብር ከፋዮች መልዕክቱ ከተላከላቸው ጊዜ ጀምሮ እስከ ነሐሴ 20 ቀን 2018 ዓ.ም ባሉት ቀናት ውስጥ ያለ ቅጣት ግብራቸውን መክፈል እንደሚችሉ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም