የኢትዮጵያ ዲጂታል መሰረተ ልማት ግንባታ ሀገሪቱ ግቧን በፍጥነት ለማሳካት የምታደርገውን ጥረት ያሳያል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዲጂታል መሰረተ ልማት ግንባታ ሀገሪቱ ግቧን በፍጥነት ለማሳካት የምታደርገውን ጥረት ያሳያል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2018 (ኢዜአ) ፦የኢትዮጵያ ዲጂታል መሰረተ ልማት ግንባታና ቀልጣፋ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ሀገሪቱ ግቧን በፍጥነት ለማሳካት የምታደርገውን ጥረት በግልጽ የሚያሳይ መሆኑን የቤኒን የዲጂታል ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስትር ማሁና አክፕሎጋን ገለጹ፡፡
በቤኒን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና ኢኖቬሽን ሚኒስትር ማሁና አክፕሎጋን የተመራ የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ የአምስት ቀን የሥራ ጉብኝት ለማድረግ ትናንት ምሽት አዲስ አበባ መግባቱ ይታወቃል።
በዚህም መሰረት ሚኒስትሩና የልዑካን ቡድናቸው በኢፌዴሪ መሶብ አገልግሎትና በፋይዳ ቨርስ ጉብኝት አድርገዋል፡፡
በቤኒን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና ኢኖቬሽን ሚኒስትር ማሁና አክፕሎጋን በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ፈጣን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሽግግር እየተደረገ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን በአጭር ጊዜ አስገራሚ የዲጂታል መሰረተ ልማት በመገንባትና ፈጣን የመንግሥት አገልግሎት ስርዓት ላስመዘገቡት ዕምርታ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያና ቤኒን መካከል ያለው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክፍተት በጋራ መፍታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ልምድ መለዋወጥ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዲጂታል መሰረተ ልማት ግንባታና ቀልጣፋ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ሀገሪቱ ግቧን በፍጥነት ለማሳካት የምታደርገውን ጥረት በግልጽ እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዲጂታል መሰረተ ልማት እያደገች መሆኑን መታዘባቸውን በመጥቀስ፤ ከዚህ መማር አጀንዳችንን ለማቀላጠፍ ያግዘናል ብለዋል፡፡
ቤኒን በሳይበር ደህንነት ያላትን ጠንካራ አቅም ከኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ለማሳደግ በአቅም ግንባታና በዕውቀት ልውውጥ በጋራ መስራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡
የፋይዳ ቨርስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዮዳሔ አርዓያሥላሴ በበኩላቸው፤ የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት ለኢትዮጵያ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል፡፡
የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት ለዲጂታል ዲፕሎማሲ አቅም ግንባታ የጎላ አበርክቶ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
በአፍሪካ ብዙ የተለመደው ከአውሮፓ ወይም ከኤዥያ የሚመጣን ስርዓት ማስተዳደር ነው ያሉት አቶ ዮዳሔ፤ ቴክኖሎጂን በራስ አቅም መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ሁሉም መገንዘቡን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የራሷን ቴክኖሎጂዎች በማፍለቅ ለሌሎች ትምህርት መስጠቷ አፍሪካውያን በራሳቸው እንዲተማመኑና ዕምነት እንዲኖራቸው ያስችላል ብለዋል፡፡
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ስያሜውንና ተልዕኮውን በመቀየር ራሱን ችሎ የመንግሥት የልማት ድርጅት ሆኖ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሥር መካተቱን አንስተዋል፡፡
ይሄውም አገልግሎቱን ከኢትዮጵያ ውጪ በማስፋት በአፍሪካ ሀገራት ጭምር የማማከርና ስርዓት የመገንባት ዕድሎችን የምናገኝበት ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
የኢፌዴሪ የመሶብ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዮናስ አለማየሁ፤ መሶብ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን አሻሽሏል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ በአንድ ዓመት ውስጥ 108 የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን በመክፈት ከ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ማገልገል ተችሏል ብለዋል፡፡
ከ220 በላይ አገልግሎቶችን በላቀ ጥራት፣ ፍጥነትና ፍትሐዊ አሰራር በመስጠት የተገልጋዮችን እርካታ 98 በመቶ ማድረስ እንደተቻለም ገልጸዋል፡፡
መሶብ የኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ የመሻገር ህልም መሆኑን ገልጸው፤ የአፍሪካ ሀገራት ልምድ የሚወስዱበትና የዲፕሎማሲ ተግባቦት የሚፈጠርበት ነው ብለዋል፡፡
የቤኒን ብቻ ሳይሆን የሌሎች ዓለም ሀገራት ጭምር አይተው የሚደነቁበት መሆኑን በማንሳት ጉብኝቱ ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘርፍ ብዙ ርቀት መጓዟን እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያውያን ኢንጂነሮችና በኢትዮጵያ ሀብት የለማ መሆኑ ኢትዮጵያውያን እውቀትና አቅማችንን አስተባብረን መስራት እንደምንችል አሳይቷል ብለዋል፡፡