ቀጥታ፡

የባህር በር የዚህ ትውልድ ብሔራዊ አጀንዳ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2018 (ኢዜአ)፦ የባህር በር የዚህ ትውልድ ብሔራዊ አጀንዳ መሆኑን የማህበራዊ ሳይንስ ምሁር ብርሀኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር) ገለጹ።

ኢትዮጵያ በታሪክም ሆነ ህጋዊ መሰረትን በካደ ሁኔታ ያጣችው የባህር በር ኢኮኖሚያዊ ዕድገቷን እንደጎዳው ምሁራን ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት እንድትሆንና ብሔራዊ ጥቅምን ማስከበር ላይ የተሄደበትን ርቀት አስመልክቶ ኢዜአ ከማህበራዊ ሳይንስ ምሁሩ ብርሀኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር ) ጋር ቆይታ አድርጓል።

ምሁሩ በቆይታቸው እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ታሪካዊ፣ ጂኦ-ፖለቲካዊና ህጋዊ መሰረትን የተከተለ ነው።

በውጭ ኃይሎች ሴራና በሀገር ውስጥ በነበሩ ውስብስብ ችግሮች ምክንያት ሀገሪቱ ያጣችውን የባህር በር ባለቤትነት ለማስመለስ የጀመረችው ህጋዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ወቅታዊ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዓለም አቀፍ የባህር ህግ ወደብ የሌላቸው ሀገራት ወደ ባህር የመድረስና የመጠቀም መብታቸውን በግልፅ እውቅና ይሰጣል ብለዋል።

ይህም ሀገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስከበርና የባህር በር ለማግኘት ለሚያደርጉት ዲፕሎማሲያዊና ህጋዊ ጥረት ትልቅ መሰረት ነው ሲሉ አክለዋል።

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን በሴራ ብታጣም ዳግም የባህር በር ባለቤት ለመሆን የጀመረችው ጥረት የህግና የታሪክ መሰረት ያለው መሆኑን አስረድተዋል።

የባህር በር ጥያቄው የኢትዮጵያን የንግድ ሚዛን ከማስጠበቅ ባሻገር፣ ለአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የጋራ ተጠቃሚነትና አስተማማኝ ሰላም የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለውም ብርሃኑ (ዶ/ር ) አክለዋል።

ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባህር በር ማግኘቷ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚኖራትን የንግድና የኢኮኖሚ ትስስር በማሳደግ ቀጠናዊ ውህደትን ያፋጥናል ሲሉም ገልጸዋል።

ብርሀኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር) የባህር በር የትውልድ ብሔራዊ ህልውና ጉዳይ መሆኑንም ገልጸዋል።

ለተግባራዊነቱም ዜጎች የፖለቲካም ሆነ ሌሎች አመለካከት ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በመተው ለሀገር ብሔራዊ ጥቅም በጋራ መቆም አለባቸው ብለዋል።

መንግስት በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መርህ የጀመረውን ጥረት ለማሳካት የሕዝብ ዲፕሎማሲ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል ሲሉም አመልክተዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የዘርፉ ምሁራን የባህር በር ለማግኘት የተጀመረውን ሀገራዊ ጥረት በምርምር፣ በታሪካዊና በህጋዊ ሰነዶች በማስደገፍ ሙያዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ መክረዋል።

የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም ለማስከበርና የባህር በር ባለቤትነትን እውን ለማድረግ አሁን የተጀመሩት ሁሉን አቀፍ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ምሁሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም