ኢትዮጵያ ንጹሕና አረንጓዴ ከተሞችን በመገንባት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት እየሆነች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ንጹሕና አረንጓዴ ከተሞችን በመገንባት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት እየሆነች ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2018 (ኢዜአ) ፦ኢትዮጵያ ከተሞቿን አረንጓዴ፣ ንጹሕና ዘመናዊ የኑሮ ማዕከላት በማድረግ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት እየሆነች መምጣቷን የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የኮሙኒኬሽን ኦፊሰር ኸርነስት ቺ ቾ ገለጹ።
ኦፊሰሩ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በአዲስ አበባ የአረንጓዴ ከተማ ፖሊሲዎች በተግባር መተግበራቸውና ሰፊ የመሠረተ ልማት ሥራዎች መከናወናቸው በከተማዋ ሁለንተናዊ ለውጥ እንዲመዘገብ አስችሏል።
በተለይም በአዲስ አበባ ጎዳናዎች፣ ፓርኮችና የሕዝብ መገልገያ ቦታዎች ላይ የታዩ ተጨባጭ ለውጦች ከተማዋን የተሻለ የኑሮ አካባቢ እንዲሆን እያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ከ10 ዓመታት በፊት ወደ አዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ መምጣታቸውን ያስታወሱት ኦፊሰሩ፣ የመንገድና የከተማ መሠረተ ልማቶች አሁን ከቀድሞው ጋር ሲነጻጸሩ እጅግ አስደናቂ ለውጥ እንዳሳዩ ገልጸዋል።
ዘመናዊ ከተማ ማለት የተሻለ ደህንነት ያላቸው መንገዶች፣ አረንጓዴ የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎችና የተሟሉ መሠረተ ልማቶች ያሉባት ከተማ ናት ነው ብለዋል።
በዚህም በአዲስ አበባ የፓርኮች፣ የሕፃናት መዝናኛ ስፍራዎችና ሌሎች የሕዝብ መገልገያዎች በስፋት መገንባታቸው የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ስኬትም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያግዙ፣ ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን የማስፋፋት ጥረቶችም ወሳኝ የለውጥ አካል መሆናቸውን አክለዋል።
ኢትዮጵያ ከተሞቿን አረንጓዴና ንጹሕ በማድረግ ለሌሎች ሀገራት አርዓያ መሆኗን ቀጥላለች ብለዋል።
በቱሪዝም ዘርፍም ኢትዮጵያ ተጨባጭ ለውጦችን በማስመዝገብ በአፍሪካ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑና ጥራታቸውን የጠበቁ በርካታ ሆቴሎች መገንባታቸው የዘርፉን ዕድገት እንደሚያሳይ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የተከናወኑ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ሥራዎች ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አርዓያ ናቸው ያሉት ኦፊሰሩ፣ የኢትዮጵያ የሆቴሎች ጥራትና ብዛት በብዙ የአፍሪካ ከተሞች ከሚታየው እንደሚልቅ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ማግኘቱን ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአፍሪካ ሞዴል የሆነ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።