ሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ለሀገራዊ መግባባትና ለጠንካራ የሀገረ መንግሥት ግንባታ መሰረት እየጣለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ለሀገራዊ መግባባትና ለጠንካራ የሀገረ መንግሥት ግንባታ መሰረት እየጣለ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2018 (ኢዜአ) ፦ሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ለሀገራዊ መግባባትና ለጠንካራ የሀገረ መንግሥት ግንባታ መሰረት እየጣለ ነው ሲሉ ተመካካሪዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱን ቀጥሏል።
በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ አራት ሺህ ወኪሎችም በስምንት ዐበይት ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ጥልቅና አሳታፊ ምክክር እያካሄዱ ይገኛሉ።
ከተመካካሪዎቹ መካከል ወጣት አብርሃም ጥላሁን ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት፤ የችግሮቻችን ምንጮች ላይ ተቀራርበን አለመወያየታችን ብዙ ዕድሎች እንዲያመልጡን አድርጓል ብሏል።
በምክክሩ ላይ በመሳተፍ የሌላውን እይታ መረዳት መቻሉን የገለጸው ወጣቱ፤ መሰል ምክክር የሀገረ መንግሥት ግንባታ እንዲጠናከር መሰረት የሚጥል መሆኑን ተናግሯል።
ሀገር የሚገነባው በኃይል ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ምክክር መሆኑን ገልጾ፤ ''ሂደቱን አሁን ጀምረናል፤ በዚህ ደግሞ ጥሩ ውጤት እንደሚመጣ እምነቴ የጸና ነው'' ሲል ተናግሯል።
ሌላው ተመካካሪ አቶ ደሱ ተፈራ በበኩላቸው፤ በዚህ ታሪካዊ የምክክር ሂደት ላይ በመሳተፋቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡
ዜጎች በአንድ ሀገር ጉዳይ ላይ መምከራቸው ብሩህ ተስፋ የሚፈነጥቅ መሆኑን ጠቅሰው፣ በሀገር ደረጃ የመጀመሪያ የሆነው የምክክር ጉባኤው ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ምክክሩ ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ እንዲተዋወቁና እንዲግባቡ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቅሰው፤ ይህ ለጠንካራ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ትልቅ መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።
ሌላው የምክክሩ ተሳታፊ አቶ አድጎልኝ መኮንን በሰጡት አስተያየት፤ በምክክር ሂደቱ የሕዝቦችን አንድነት የሚያጠናክሩ ሂደቶችን እየተመለከቱ መሆኑን ጠቁመዋል።
የምክክር ሂደቱ እጅግ አበረታች መሆኑን ጠቅሰው፣ ከሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የተሰበሰቡ ተወካዮች የኢትዮጵያን የጋራ ጥቅም አስቀድመው በጋራ ሲመክሩ መመልከት ትልቅ ደስታና ተስፋ የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ምክክሩም ውጤት እያመጣ መሆኑን እስካሁን ከተመለከቱት ሂደት መመልከት መቻላቸውን ጠቅሰው፤ ይህ ለኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ መሆኑን ጠቅሰዋል።